የድሬዳዋ ነዋሪዎች የሕዳሴው ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ተሳትፏቸውን ለማጠናከር ተነሳስተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ ነዋሪዎች የሕዳሴው ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ተሳትፏቸውን ለማጠናከር ተነሳስተዋል
ድሬዳዋ ፤ ነሐሴ 22/2013 (ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው ለመቀጠል መነሳሳታቸውን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ተናገሩ።
ነዋሪዎቹ "ግድቡ ለወጣቱ፤ ወጣቱ ለግድቡ" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአደባባይ የድጋፍ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተሳተፉት ነዋሪዎች ግድቡ እንደሀገር ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝና የሚያፋጥን መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ እንዳለ ክንፈ ፤ ግድቡ ልማትን በማፋጠን የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
"ሃብታችንን አልምተን ለመጠቀም የሚከለክልን የለም" ያሉት አቶ እንዳለ፣ አንድነትን በማጽናት ግድቡን ዳር ለማድረስ የሚደረገው ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።
ግድቡ በዓለም አደባባይ ከፍ የሚያደርገን የማንነታችንና የአንድነታችን መገለጫ ሀብታችን ነው" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ በላይነሽ ከበደ ናቸው።
የሕዳሴው ግድብ የግንባታ ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለግድቡ ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው ለቀጠል መነሳሳታቸውን ተናግረዋል፡፡
አቶ ምነውየለት ደግአረገ በበኩላቸው፤ በደመወዛቸው ለግድቡ የተዘጋጀውን ቦንድ ከመግዛት በዘለል በልጆቻቸው ስም ለግድቡ ድጋፍ ማድረጋቸውን ነው ያስታወቁት።
ግድቡ ዕውን እንዳይሆን ከውጭ እና ውስጥ የተነሱትን ጠላቶች በተባበረ ክንድ መመከት እንደሚገባ አመልክተው፤ ለግድቡ የጀመሩትን ድጋፍ በቀጣይም እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል፡፡
በድጋፉ ሰልፉ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ፤ በራስ ገንዘብና ጉልበት እየተገነባ ያለው የህዳሴው ገድብ እየተገባደደ መሆኑን አመልክተዋል።
ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀመር ከሚኖረው ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ዕድገት በተጨማሪ የወጣቶችን ተስፋ እንደሚያለመልምም ተናግረዋል፡፡
"የሀገር ተስፋና ምልክት የሆነው የሕዳሴ ግድብ ዕውን እንዲሆን በተለያዩ የውጭና የውስጥ አካላት እየተፈጸመ ያለውን ጫና በአንድነት መከላከል ይገባል" ብለዋል፡፡
በድሬዳዋ ታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የህዝብ ተሣትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ከድር ጁሃር ፤ ነዋሪዎች እያደረጉ ላለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አመስግነው፣ "በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ብለዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ ሥራ ከተጀመረ ወዲህ በቦንድ ግዥ ብቻ ከ81 ሚሊዮን ብር በላይ ከህብረተሰቡ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
ዘንድሮ ለግድቡ ግንባታ ከ3 ሚሊዮን 700 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ መደረጉም ተመልክቷል።