ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሓትን መደገፍ ከኢትዮጵያ ወንድሞቻችን ከመነጠል ውጪ የሚያመጣው ፋይዳ የለም-የትግራይ ተወላጆች

ነሀሴ 22/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓትን መደገፍ "ከኢትዮጵያ ወንድሞቻችን ከመነጠል ውጪ የሚያመጣው ፋይዳ የለም" ሲሉ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ።

ቡድኑ የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ለመነጠል የሚያደርገው እንቅስቃሴ እንዲገታም ራሱ ህዝቡ የሚጠበቅበትን ሚና መወጣት እንዳለበትም ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል።

አሸባሪው ህወሓት አገርን ለማፍረስ የሄደበት ርቀት፣ በነበረው የሥልጣን ጊዜ በዜጎች ላይ ያደረሰው ግፍና በደል ላይ ውይይት ተደርጓል።    

በተለይም በአጎራባች አፋርና አማራ ክልሎች የሚፈጽማቸው ትንኮሳዎችና የንጹሃን ግድያዎች ቡድኑ የትግራይ ህዝብ ሰላም እንዳይኖረው ጽኑ ፍላጎት ያለው መሆኑን አመላካች እንደሆነ ነው የተነሳው።

ከውይይት ተሳታፊዎቹ መካከል አቶ ካሳሁን ገብረሥላሴ እንደገለጹት፤ አሸባሪው ቡድን የትግራይ ህዝብን አይወክልም የሚለው የሚያስማማ ነው።    

ጦርነቱ በተካሄደባቸው ስምንት ወራት ውስጥ "መንግሥት በሆደ-ሰፊነት ማድረግ የሚገባውን ሁሉ አድርጓል" ያሉት አቶ ካሳሁን፤ ማህበረሰቡ እንዳይጎዳ ያደረገው ጥንቃቄ መንግሥትን ሊያስመሰግ ነው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።   

ይህንን አሸባሪ ቡድን በመደገፍ የምናመጣው ለውጥ የለም፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ ከመነጠል ውጭ ሲሉም ነው የተናገሩት።   

ሌላው የክፍለ ከተማው ነዋሪ አቶ ያሬድ ተፈራ በበኩላቸው የአሸባሪው ህወሓት አቋም "እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ" የሚል የሥልጣን ጥያቄ መሆኑን ሁሉም መገንዘብ ይኖርበታል።  

የትግራይ ህዝብ እስከመቼ ነው እየተማገደ የሚኖረው? ሲልም ይጠይቃል።

የክፍለ ከተማው ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተካ አባይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሓት የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ለማጋጨት ብዙ ርቀት እየተጓዘ ነው።  

"የአሸባሪው ህወሓት ቡድን ለትግራይ ህዝብ ምንም አልጠቀመም" ያሉት ኃላፊው፤ የትግራይ ተወላጆች ይህንን ጉዳይ በመገንዘብ መታገል እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ቡድኑ የትግራይ ህዝብን አንገት የሚያስደፋ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተካ በማይካድራ፣ በአፋርና በሰሜን ወሎ ያደረሳቸው ጥፋቶች ለዚህ ማሳያዎች ናቸው ሲሉም አብራርተዋል።

ቡድኑ ትግራይን ለመገንጠል እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ኃይል ከዚህ በላይ እንዳይጓዝ ህዝቡ "በቃ! ከዚህ በኋላ አይሆንም ሊለው ይገባል" ነው ያሉት።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም