ቀጥታ፡

በቪትስ መኪና አምስት ክላሽንኮቭ ከ132 ጥይት ጋር ሲያጓጉዙ የነበሩ ግለሰቦች ተያዙ

ጎንደር፣ ነሐሴ 22 ቀን 2013(ኢዜአ) ቪትስ በሚል ስያሜ በሚታወቅ በቤት መኪና ውስጥ በህገ-ወጥ መንገድ አምስት ክላሽንኮቭ ከ132 ጥይት ጋር ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎችን መያዙን የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዋና ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ኢየሩስ አስማረ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ትናንት ምሽት አንድ ሰዓት በከተማው ልዩ ስሙ አየር ጤና በተባለው አካባቢ ነው፡፡

ግለሰቦቹ የሰሌዳ ቁጥሩ A76390 አዲስ አበባ በሆነ ቪትስ የቤት መኪና ውስጥ አምስት ክላሽንኮቭ ከ132 የክላሽ ጥይት እና 43ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ በድብቅ ሲያጓጉዙ መንገድ ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ሊያዙ ችለዋል፡፡

አሽከርካሪውን ጨምሮ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ፖሊስ ምርመራ መጀመሩን ኢንስፔክተር ኢየሩስ አስታውቀዋል፡፡

“በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያና ገንዘብ ለጥፋት ተልእኮ ለሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ተልዕኮ ማሳኪያ ሊውል እንደሚችል ፖሊስ ጥርጣሬ አለው” ብለዋል፡፡ 

ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የአካባቢን ሰላምና የህዝቦችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ወንጀል በመሆኑ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር የጀመረውን ግንኙነት አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም