ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ

ገዛኸኝ ደገፉ /ኢዜአ/

የአፍሪካ ቀንድ ከህንድ ውቅያኖስ አንስቶ ቀይ ባህር እና ሜዲትራኒያን ባህር የሚያያዙበት አካባቢ የሚገኝ እንደመሆኑ የዓለማችን ልእለ ሃያላን ሀገራት በስትራቴጂያዊ ጠቀሜታው ትኩረት እንዲሰጡበት አድርጓቸዋል። የአረብ ሀገራትም በአካባቢው ላይ የበላይነትን ለመያዝ ባላቸው ፍላጎት በቅርበት ይከታተሉታል። የአፍሪካ ቀንድ ባለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ሀያላኑ ሀገራት በአካባቢው የጦር ካምፕ ለማቋቋም በሚያደርጉት ፉክክር ለበርካታ አስርት አመታት ያልተረጋጋ እንዲሆን አድርጎታል።

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር እና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ በምታበረክተው ጉልህ አስተዋጽኦ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ትታወቃለች። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተልእኮ መወጣት የጀመረችው በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ነው። የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይል በኮሪያና በኮንጎ ያደረጋቸው አኩሪ ተግባራት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በስፋት ይታወቃል።

በሩዋንዳ፣ በብሩንዲ እንዲሁም በላይቤሪያ ተሰማርቶ የነበረው የሰላም አስከባሪ ሃይል ባሳየው መልካም ስነምግባር እና ተልእኮውን በብቃት በመወጣት በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትና ተወዳጅነት አግኝቶ እንደነበር የተለያዩ ዘገባዎች ያመለክታሉ። በተመሳሳይ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን እና በሱዳን ሰላም ማስከበር ኢትዮጵያ ሚናዋን በብቃት ተወጥታለች።

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልእኮ በአፍሪካም ይሁን ከአፍሪካ ውጪ ባላት መልካም ዝና የተነሳ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቀጠናው አካባቢ የጎላ አስተዋጽኦ እንደምታበረክት ይታሰባል። ይህም በመሆኑ ከብዙዎቹ ሀያላን ሀገራት ጋር በመልካም ወዳጅነት እንድትታወቅ አድርጓታል። ይህም በመሆኑ የኢትዮጵያ መረጋጋት ለአፍሪካ ቀንድ ብሎም ለመላው አፍሪካ ሀገራት ያለው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።

ሙሉጌታ ተስፋዬ የተባሉ ምሁር ከሁለት አመታት በፊት “Ethiopia’s role in the horn of Africa for promoting peace and security“ በሚል ርእስ ባስነበቡት የጥናት ጽሁፍ ላይ በቀጠናው ሀገራት ዘንድ የኢትዮጵያ ሚና የማይተካ መሆኑን አብራርተዋል። የአፍሪካ ቀንድ የተለያዩ ታጣቂዎች የበዙበት አካባቢ ከመሆኑም ባሻገር ከግጭት ነፃ ሆኖ አያውቅም የሚሉት የጥናት ጽሑፍ አቅራቢው፤ ሽብርተኝነት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ለዓመታት ፈተና ሆነው እንደዘለቁ ይገልጻሉ። ኢትዮጵያ በቀጠናው ባላት የተሻለ ስምና ታሪክ እንዲሁም በህዝብ ብዛቷና በጠንካራ ወታደራዊ አቅሟ ለአካባቢው መረጋጋት ቁልፍ ድርሻ ታበረክታለች ሲሉም ገልጸዋል።   

ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ በተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ለረጅም ጊዜያት በዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የነበረችው ሶማሊያን ጨምሮ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተፈጠረው ሰላም ዓለምን አነጋግሯል። ይህ የሶስቱ ሀገራት መልካም ግንኙነት የቀጠናው አካባቢ ማህበረሰብ ለረጅም ዓመታት የናፈቀው ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ ተስፋ ተጥሎበታል። በሶስቱ ሀገራት መካከል የተጀመረው መልካም ግንኙነት እየተጠናከረ ከሄደ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች ፈጣን እድገት እንደሚያመጣ ምሁራን ይገልጻሉ።  

የሶስቱን ሀገራት ግንኙነት በስጋት የተመለከቱት አንዳንድ ሀገራት ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዳይቀጥል ለማስተጓጎል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሲሰሩ ይስተዋላል። እነዚህ ሀገራት በተለያየ መልኩ ለአሸባሪው ህወሓት ድጋፍ ማድረግ ከጀመሩ ውሎ አድሯል። ቡድኑ ለበርካታ ዓመታት ኢትዮጵያን በመከፋፈል ሲሰራ የቆየ ሲሆን በህዝብ ግፊት ስልጣኑን ለመልቀቅ ከተገደደ በኋላ በትግራይ መቀሌ መሽጎ ኢትዮጵያን በማተራመስ ችግሩን ወደ ቀጠናው ሀገራት ለማዛመት ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል።

ቡድኑ በሰራቸው ሴራዎች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሚሊዮኖችን ከቤት ንብረታቸው በማፈናቀልና በሺዎች የሚቆጠሩትን በመግደል መረጋጋት እንዳይፈጠር አድርጓል። በመጨረሻም ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ በሌሊት ጥቃት በመፈጸም ሀገር ለማተራመስ ሞክሯል።

ይህን ተከትሎ መንግስት በወሰደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ሀገሪቱ ተደቅኖባት ከነበረው አደጋ መላቀቅ የቻለች ቢሆንም አሁንም በህወሓት የሽብር ቡድን የሀገር ሉዓላዊነትን የሚፈታተን ትንኮሳ አልቆመም።ጉዳዩን በቅጡ ያልተረዱ አሊያም የፖለቲካ ትርፍ በሚያሰሉ የውጭ ሀገራት ለአሸባሪውን ቡድን በመወገን የተለያዩ ጫናዎች እየፈጠሩ ይስተዋላል።

ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የፖለቲካና የውጭ ግንኙነት ምሁራን እንደሚገልጹት በተነጻጻሪ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋና ለሰላም ማስከበር ተልእኮ እምነት የተጣለባት ኢትዮጵያ ካልተረጋጋች በቀጥታ የአፍሪካ ቀንድን ስጋት ላይ ከመጣል አልፎ ውጤቱ ለአህጉሩ ሊተርፍ እንደሚችል በአጽንኦት ይናገራሉ። ይህን የተገነዘቡ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገራት አሁን ያጋጠማትን ችግር በጥንቃቄ እንዲፈታ የፈልጋሉ።

ሰሞኑን የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ ባካሄደው ስብሰባ ላይ እንደ ቻይና፣ ህንድ እና ሩሲያ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አስረድተዋል። በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ለማምጣት በኢትዮጵያ በእራሷ የሚመራና በሕገ መንግሥቷ ማዕቀፍ ውስጥ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መረጋጋት ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ብሎም ሽብርተኝነት እንዳያንሰራራ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በቀላል የሚገመት አይደለም። ስለሆነም በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን የሚመኙ ሀገራት ሁሉ ለኢትዮጵያ መረጋጋት አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል።      

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም