የውሃ ሀብትን በዘላቂነት ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ ነው...የተፋሰስ ልማት ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የውሃ ሀብትን በዘላቂነት ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ ነው...የተፋሰስ ልማት ባለስልጣን
አዳማ፤ ነሐሴ 22/2013 (ኢዜአ) የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም የአሠራር ስርዓት በመዘርጋት የውሀ ሀብትን በዘላቂነት ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራ መሆኑን የተፋሰስ ልማት ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ በጉዳዩ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ባካሔደው የምክክር መድረክ ላይ የውሃ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አብረሃ አዱኛ እንደገለጹት ውሃና መሬትን አቀናጅቶ ለመጠቀም የሚያስችል የአስተዳደርና የአመራር ስርዓት እውን ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል።
እየጨመረ ካለው የህዝብ ቁጥርና የከተሞች መስፋፋት ጋር በተገናኘም በቀጣይ ዓመታት የውሃ እጥረት እንዳይፈጠር የውሃ ሀብትን ማልማትና በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያስችል ዘመናዊ አስተዳደርና አሰራር መዘርጋት ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከ122 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የገፀ ምድር ውሃ ያላት ሲሆን የከርሰ ምድር የውሃ ሀብቱን መጠን ለማወቅ ጥናቶች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ ውሃን በቁጠባ መጠቀምና አገልግሎት ላይ ለማዋል የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃን ከብክነት መጠበቅና ሀብቱን ማልማት አለብን ብለዋል።
እየተከናወነ ያለውን የመስኖ ልማት፣ የሃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታና ዘለቄታዊ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የመጠጥ ውሃ፣ ቀጣይ ሊኖር የሚችለው የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ ለመቋቋም ውሃን በእቅድ መጠቀም የሚያስችል የጋራ የተቀናጀ ስርዓትና አመራር መዘርጋት ግዴታ መሆኑንም አመልክተዋል።
በዚህም የውሃ መረጃ ስርዓት በተለይ የውሃ ተጠቃሚዎች፣ ፍጆታና ዘላቄታዊነት ተፋሰሶችና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲያቅዱና በጋራ የሀብቱን ልማት እንዲያከናወኑ ለማስቻል እንደሆነም ተናግረዋል።
የተፋሰሶች ልማት ፕሮጄክት በመቅረፅ የሃይል ማመንጫዎች በደለል እንዳይሞሉ፣ ሃይቆች ከመጤ አረም መጠበቅና ተፈጥሮን መሰረት ባደረገ መልኩ እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑን ሚንስትር ዴኤታው ገልፀዋል።
የአካባቢው ህብረተሰብ፣ ባለሃብቶች፣ መንግስትና ሌሎች በዘርፉ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውሃ ሀብት ምደባ፣ ምዝገባ፣ ስርጭትና አጠቃቀም ስርዓት እውን እየሆነ ይገኛልም ነው ያሉት።
የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ ህብት ጥናት እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት ዶክተር አብረሃ፤ ለውሃ ተጠቃሚዎች ፍቃድ የመስጠት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
መድረኩንም የውሃ ሀብት አስተዳደርና የአጠቃቀም አመራር ስርዓት በመዘርጋት ሀብቱን በዘላቂነት ለመጠቀም እንዲቻል ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድ ናቸው።
የአባይ፣ ስምጥ ሸለቆና የአዋሽ ተፋሰሶች የውሃ ሀብቱን በዘላቂነት ለማልማት የሚያስችል ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ በተለይ የውሃ ሀብቱን መጨመር፣ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ዙሪያ የአፈርና ውሃ እቀባ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የሚሰሩ የተፋሰስ ልማቶች የውሃ ሀብት ልማቱን የጋራና የተቀናጀ ለማድረግ እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑንም አመልክተዋል።
ለሁለት ቀናት በተካሔደው መድረክ ላይ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የውሃ ሴክተር፣ በውሃ ዘርፍ የሚሰሩ ተቋማትና ድርጅቶች ተሳትፈዋል።