በደቡብ ክልል ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ ነው
ሀዋሳ ነሀሴ6/2010 በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች ሳቢያ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም ኮሚቴ ተዋቅሮ ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ። የተቋቋመው የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ እስካሁን ድረስ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖችና በክልሉ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምራት ዲላ እንዳሉት የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴው በክልል ውስጥ፣ ከክልሉ ውጪና በውጪ አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አንድ ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ እስካሁን ድረስም የክልሉና የፌዴራል መንግስት እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለተፈናቃዮቹ የዕለት ደራሽ እርዳታ እያደረጉላቸው ይገኛሉ። ከእዚህ በተጨማሪ ዜጎቹ ወደ ቀያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ለማድረግ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የመንግስት ሠራተኞችና ነዋሪዎችም የተለያዩ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡ ለእዚህም የእንስሳትና አሳ ሀብት ልማት ቢሮ፣ የውሃ ሀብት ቢሮ፣ የመስኖና ኢነርጂ ኤጀንሲ ሠራተኞች ከወር ደመወዛቸው 50 በመቶ መለገሳቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ፣ የሴቶችና ህጻናት ቢሮ፣ የስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ የክልሉ ምክር ቤት ሠራተኞች ከወር ደመወዛቸው 25 በመቶ መለገሳቸውንም አመልክተዋል፡፡ አቶ ታምራት እንዳሉት ሠራተኞቹ ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ በቁሳቁስና አልባሳት ድጋፍ እያደረጉ ሲሆን የክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች፣ ኮምፒውተሮችና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመሸጥ ለተፈናቃዮቹ ማቋቋሚያ ገቢ እንዲሆን መወሰናቸውንም ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር 15 ሚሊዮን ብር፣ ወጋገን ባንክ 5 ሚሊዮን ብር፣ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም 1 ሚሊዮን ብር የስልጤ ዞን ሰገን አካባቢ ህዝቦች ፣ ከንባታ ጠንባሮ እና ሀድያ ዞኖች ከአንድ አስከ ሁለት ሚሊዮን ብር መስጠታቸውንም አመልክተዋል፡፡ "የተለያዩ አካላት በሰጡት ድጋፍ እስካሁን ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተሰብሰቧል" ብለዋል፡፡ ህብረተሰቡ ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን በመረዳት ተፈናቃዮቹን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም አቶ ታምራት ጥሪ አቅርበዋል። ድጋፍ ለማድረግ የሚፈልጉ አካላትም ለእዚህ ተብሎ በተከፈተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሒሳብ ቁጥር 1000251170898 ገንዘብ ማስገባት እንደሚችሉ አቶ ታምራት አመልክተዋል፡፡