የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቀነስ የገቢ ንግድ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት መደረግ አለበት -ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቀነስ የገቢ ንግድ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት መደረግ አለበት -ምሁራን

ኢአዲስ አበባ ነሀሴ 6/2010በኢትዮጵያ ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቀነስ የገቢ ንግድ ተኪ ምርቶች ላይ ማተኮር እና የአገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ባህልን ማጎልበት እንደሚገባ የምጣኔ ኃብት ምሁራን ገለጹ። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ ወደ አገር ቤት ሲልኩ ህጋዊውን መንገድ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠር አንደሚገባም ምሁራኑ መክረዋል። ኢትዮጵያ ከወጭ ንግዷ ይልቅ ከውጭ የምታስገባው ምርት ከፍተኛ በመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲገጥማት ይስተዋላል። ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት አገሪቱ ከውጭ ንግድ ያገኘቸው የውጭ ምንዛሪ መጠን ሶስት ቢሊዮን ዶላር አይሞላም። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በ2009 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ የተገኘው 2 ነጥብ 9 ቢሊዬን ዶላር ሲሆን አሁን በተጠናቀቀው በጀት ደግሞ 2 ነጥብ 83 ቢሊየን ዶላር ብቻ ነው። በተለያዩ የውጭ አገራት ይኖራሉ ተብለው ከሚታሰቡት ኢትዮጵያዊያን መካከል አስከ 80 በመቶ የሚሆኑት ለዘመድ አዝማድ ብለው የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ቤት የሚልኩት ህጋዊ ባልሆነ መንገድ መሆኑም ይነገራል። መንግስት በአገሪቷ የሚታየውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማሻሻል በሚል ተግባራዊ ያደረገው የብር የመግዛት አቅም መቀነስ እርምጃ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ አላመጣም። የምጣኔ ኃበት ምሁራን ለኢዜአ እንደተናገሩት በአገሪቱ የሚታየውን የውጭ ምንዛሪ ችግር ማቃለል የሚቻልባቸው ሁነኛ እርምጃዎች የህብረተሰቡን የአገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ባህል ማዳበር፣ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶችን አቅም ማጠናከርና ማበረታታት እንደዚሁም ከዲያስፖራው ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር ናቸው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ስራ ትምህርት ቤት የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ጊዲሳ ለቺሳ እንዳሉት፤ መንግስት የወጭ ንግዱን የሚያበረታታውን ያህል የገቢ ንግዱን ተኪ ለሆኑ ምርቶችም አጽንኦት መስጠት አለበት። በኢትዮጵያ ያለው አብዛኞቹ ባለሃብት ሳይደክም በአጭሩ መክበር የሚፈልግ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጊዲሳ፤ አሁን ያለው ብዙው ባለኃብት ከማንፋክቸሪንግ ይልቅ የአገልግሎት ዘርፉን እንደሚመርጥ በጥናት አረጋግጫለሁ ብለዋል። የውጭ ምንዛሪ አቅምን በዘላቂነት ማሳደግ ይቻል ዘንድ መንግስት የማምረቻ ዘርፉን ለማስፋፋት ጠንከር ያለ ህግና የአፈፃፀም መመሪያ ማዘጋጀት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል። በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዲን ዶክተር ካሳ ተሻገር የአገሪቱን የምንዛሬ እጥረት ለመቀነስ የተለያዩ አገራትን ተሞክሮ መውሰድ ይገባል ሲሉ ነው አፅንኦት የሰጡት። ዘይት፣ ስኳርና መሰል ሸቀጦችን በበቂ ሁኔታ በማምራት ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለወጭ ንግድ መጠቀም የሚቻልበት ሁኔታ በስፋት ያለ ቢሆንም አገሪቱ ግን ዛሬም እኒሀን ሸቀጦች በውጭ ምንዛሪ ከውጭ መግዛቷን ቀጥላለች፤ የአገር ውስጥ ምርትን በማበረታታት የወጪና ገቢ ንግዱን ማመጣጠን አልቻለችም ብለዋል። ዜጎች በአገራቸው ምርት የመጠቀም ልምዳቸውን በማጎልበት የልማት አጋዥ እንዲሆኑ መንግስትና ምሁራን በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል ዶክተር ካሳ። በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከመንግስት ጋር በነበራቸው አለመግባባትም አገሪቱ በውጭ ከሚኖሩ ዜጎቿ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ሳታገኝ ቆይታለች ሲሉም ዶክተር ካሳ ገልፀዋል። በመሆኑም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ዜጎች ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ወደ አገር ቤት ገንዘብ ሲልኩ ህጋዊውን የመላኪያ መንገድ እንዲጠቀሙ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋት አንዳለበትም ምሁሩ አስገንዝበዋል። አሁን የተከፈተውን የዲያስፖራ ትረስት ፈንድን ጉልህ ጠቀሜታ በማውሳት። በቀጣይም ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ምሁራን ገለልተኛ ሆነው ለፖሊሲ ድጋፍ የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማቅረብ መንግስት የቀረቡለትን የምርምር ውጤቶች ተቀብሎ በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በ2009 ዓ.ም በውጭ አገራት ከሚኖሩ ዜጎች ወደ አገር ቤት የተላከው 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ነው። ይህ የውጭ ምንዛሪ መጠን በህጋዊው መንገድ ወደ አገር ቤት የተላከው ሲሆን ከዚህ ውጭ ያለውና አስከ 80 በመቶ የሚደርሰው የውጭ ምንዛሪ የሚላከው ግን መደበኛ እና ህጋዊ ባልሆነው የገንዘብ ማሰተላለፊያ ስርዓት ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ በዚህ መንገድ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን ከአብዛኛው የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነፃፀር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑም ይነገራል።