ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ሃገራዊ አንድነት የሚደራደር ህዝብም መንግስትም የለም…ዶክተር አብርሃም በላይ

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 21/2013 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ ሉኣላዊነትና ሃገራዊ አንድነት ላይ የሚደራደር ህዝብም ሆነ መንግስት የለም ሲሉ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።

ዋና ስራ አስፈጻሚው እንዳሉት የኢትዮጵያ ቀጣይ የልማት እድገት፣ የህዝቡ አንድነትና የመንግስት ጥንካሬ ያስጨነቃቸው አንዳንድ የውጭ ሃገራት ጣልቃ በመግባት ያሏትን የምትፈፅም አቅመ ቢስ ሃገር ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረትም ተቀባይነት የለውም። 

በየጊዜው የውስጥና የውጭ ሃይሎችን በመጠቀም የሃገርን ሉዓላዊነትና አንድነት ለመፈታተን በሚያደርጉት ጥረትም እንደ አሸባሪው ህወሃት ያሉ ጸረ-ህዝብ ቡድኖችን እየተጠቀሙ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ሰላምና ሃገራዊ አንድነት ላይ ለመወሰንና የሰጡንንም እንድንቀበል ለማድረግ በማያገባቸው ጉዳይ ለመግባት የሚሞክሩ የውጭ ሃይሎችን መታገስ እንደማይቻል ገልጸው ይሄንን የሚቀበል ህዝብም ሆነ መንግስት እንደሌለ አስረድተዋል።

“ማንኛውም ሃይል መጥቶ በጉልበት ሃገርን የመግዛት ሃገርን የማተራፈስ አጀንዳ ማግኘት የለበትም” ያሉት ዶክተር አብርሃም ሃገርንና መንግስትን የመቀየር ስልጣንም የለውም በቁማችን የምናየው ልንቀበለውም የምንችለው አይደለም” ብለዋል።

እነዚህ ሃይሎች የመንግስት አካሔድ እየገባቸው መሆኑን ገልጸው የኢትዮጵያዊያን አንድነትና ልማት የሚያስጨንቃቸው ሃይሎች ሁሌም በልዩነትና በትርምስ እንድንኖር እንደሚፈልጉም ገልጸዋል።

''እኛ ሁሌም በድህነት ውስጥ እንድኖር፣ ሁሌም በልዩነት እንድንኖር፣ ሁሌም በትርምስና ብጥብጥ እንድንኖር የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ተቀናጅተው እየሰሩ ይገኛሉም''ብለዋል።

ኢትዮጵያ በልማት ወዴት እየሄደች እንደሆነ፣ የለውጡ መንግስት በጉልበትና በሉአላዊነት ለመጣ ማናቸውም ሃይል ድርድር እንደማይቀበል የገባቸው ሃገራት አሁንም ያለማቋረጥ ለጥፋት እየሰሩ እንደሚገኙም አስረድተዋል።

ሃገራችንን በየጊዜው ለፈተና ከሚዳርጓት ጉዳዮች አንዱና ዋናው ደግሞ የውስጥ ሃይሎች የጥፋት ተልዕኮ መሆኑን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው ለህዝብ አስቦ የማያውቀው አሸባሪው ህወሃት የዚህ ማሳያ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ይሄንን አሸባሪ ቡድን በመደገፍ በውጭም ሆነ በሃገር ውስጥ ሆነው የኢትዮጵያን ጉዳይ አጀንዳ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሃገራት ለጥቅማቸው የሚመች መንግስት ከመፈለግ አንፃር የተለያዩ ተጽዕኖዎችን ለመፍጠር መሞከራቸው አዲስ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።

ቡድኑ ህዝብና ሃገርን የካደ ክህደቱንም የተከበረውንና የህዝብ ደጀን የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት በመድፈር በተጨባጭ ያረጋገጠ እንደሆነም ገልፀዋል።

ከዚህ በፊትም በድብቅና በሴራ የክህደትና ሃገር የማፍረስ ፣ ህዝብ የመበደል አጀንዳዎችን ይዞ ሲሰራ የኖረ እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን ላይ እንቅስቃሴውን ሁሉ በይፋ ማድረጉ እንጂ ከቀደመ ባህሪው የተለየ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ስለሆነም ይህ አሸባሪ ቡድን የሸረበው አገር የማፍረስ አጀንዳ እንዲቆም ብቻ ሳይሆን ለዘላለም እንዲጠፋ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች በጋራ ተጠናክረው ይቀጥላሉም ብለዋል።

“የህውሃት ሸባሪ ቡድን ሃገር ለማተራመስና ለማፍረስ ሆን ብሎ የተነሳ ሽብርተኝነቱንም በይፋ ያወጀ ቡድን ነው” ያሉት ዶክተር አብርሃም ይሄንን ተከትሎ አሁን ላይ በሃገራችን ሉአላዊነትና አንድነት ላይ ጫና ለመፍጠር በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች የሚደረገውም መቼም እንደማይሳካ ጠቅሰዋል።
በሃገራችን የውስጥ ጉዳይ ዙሪያ የመከረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ቻይና ፣ሩሲያ፣ ህንድ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን በራሷ መፍታት እንደምትችል በመግለጽ አጋርነታቸውን ማሳየታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም