ቀጥታ፡

በጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ አገራት ዓለም አቀፍ መርህን የተከተለ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 21/2013 (ኢዜአ) በጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ አገራት ሕጋዊነትና ዓለም አቀፍ መርህን የተከተለ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕግ ምሁራን ገለጹ።

በተቃራኒ የቆሙ አገራት አቋም ግን ግልጽ አድሏዊነት ያንጸባረቁበትና ኢትዮጵያ የያዘችውን እውነታ የካደ መሆኑን ተናግረዋል።

ምድረ ቀደምት ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በቀጥታ ወረራ የፈጸሙባት እንዲሁም በስውር ተልዕኮ እንድትዳከም መልከ ብዙ ጫና ያደረጉባት የውጭ ሃይሎች መሆናቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች በተጋረጡባት ወቅት አጋጣሚውን በመጠቀም ሕልውናዋን ለማናጋት የተሰለፉ አገራት እንዳሉ ሁሉ ፍትህና ሐቅ ከያዘችው አገር ጎን የቆሙም የቁርጥ ቀን ወዳጆች ነበሯት።

የዓለም አገራት ማህበር የሆኑት ሊግ ኦፍ ኔሽንና የኋለኛው የተባበሩት መንግስታት መድረክ ላይ የግፍ ወረራ የተፈጸመባት ኢትዮጵያ ፍትህ በጠየቀች ጊዜ ከፋሺስቶች ጎን ቆመው ማዕቀብ የጣሉባት ኅይላትም ነበሩ።

አሸባሪው የሕወሃት ቡድን ዛሬም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ጥቃት በመፈጸሙ ኢትዮጵያ በጀመረችው የሕልውና ትግል ጣልቃ ገብተው መፈትፈት የሚሹ ኅይሎች ጉዳዩን በተደጋጋሚ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ወስደውታል።

ትናንት ምሽት በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጸጥታ ጉዳይ ላይ ምክክር ሲደረግ ከተለምዷዊ ጸረ-ኢትዮጵያ አቋሞች እንዳሉ ሁሉ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ ወዳጆችም ነበሩ።

በዚህም ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ካላቸው የምክር ቤቱ አገራት ቻይና እና ሩሲያ እንዲሁም ከተለዋጭ አባል አገራት ህንድና ጎረቤት አገር ኬኒያ የኢትዮጵያ ዕውነት ጎን የቆሙ አገራት ነበሩ።

የሕግ ምሁር አቶ ታምሩ ወንድማገኘሁ በስብሰባው የኢትዮጵያን ዕውነት በተጻረረ አቋም የተሰለፉ ምዕራባዊያን በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትና ሉዓላዊነትን የተፃረረ እንደሆነ ይገልጻሉ።

በአንዲት አገር ሉዓላዊነት ጣልቃ መግባት ከዓለም አቀፍ ሕግ ያፈነገጠ ቢሆንም 'ልዩ ሃይልና መከላከያ ከዚህ ይወጣ፤ ከአሸባሪ ጋር ተደራደሩ' የሚሉ ሃይሎች ግልፅ ጣልቃ ገብነት ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን 'ፀጥታ ጉዳይ በአፍሪካ ህብረት አልፎ ለጸጥታው ምክር ቤት መሰጠት እንዳልነበረበትም ገልፀዋል።

በትናንትናው ዕለት በተደረገው የምክር ቤቱ ስብሰባ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ ወዳጅ አገራት አቋም የሕጋዊነት ስርዓት የተከተለ፣ የሉዓላዊነትን መብት ያሳየ እንደነበር ገልጸዋል።

በአንጻሩ ሌሎች ሃይሎች ደግሞ ኢትዮጵያን 'የተበዳይ ካሳ ከፋይ' ሊያደርጉ እየጣሩ ስለመሆኑ አንስተዋል።

የሕግ ባለሙያው አቶ ገበያው ስማቸው፤ የፀጥታው ምክር ቤት አሸባሪው ሕወሃት ለ27 ዓመታት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችና ግፎችን ሲፈጽም፤ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ሲፈጽም ምዕራባዊያን አላወገዙም ይላሉ።

በአንጻሩ የምዕራባዊያን ሃይሎች በሰብዓዊ መብት ጥሰትና እርዳታ አቅርቦት ሰበብ የግል ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም በኢትዮጵያ ላይ ጫና እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በምዕራባዊያን የተንጸባረቀው አቋም ሉዓላዊነትን የጣሰ፣ በዓለም አቀፋዊ መርህ የተቃረነ ግልጽ አድሏዊነት ያለበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህም አቋም በታሪክም ኢትዮጵያ በግፍ ስትወረርና ፍትሕ ስትጠይቅ እነዚህ ሃይሎች ከግፈኞች ጋር መቆማቸውን የፋሺስት ኢጣሊያን ወረራን ለአብነት አስታውሰዋል።

በጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ ወዳጅ አገራት ማለትም ቻይና፣ ሩሲያ፣ ሕንድና ኬኒያ ያንጸባረቁት አቋም ህጋዊነትና ዓለም አቀፋዊ መርሕን የተከተለ መሆኑን ተናግረዋል።

ወዳጅ አገራቱ በውስጣዊ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባትን መቃወማቸው ብሎም ቅቡልነት ያለው መንግስት በውስጥ ጉዳይ ህግ ማስከበር፣ በወሰንና የአስተዳደር ጉዳይ በራሱ መወሰን አለበት የሚል ትክክለኛ አቋም አንፀባርቀዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም