ቀጥታ፡

በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ወዳጅነታቸውን ያሳዩ ሀገራት በታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ናቸው - ምሁራን

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 21 ቀን 2013 (ኢዜአ) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታ ምክር ቤት ትናንት የኢትዮጵያን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ በመከረ ስብሰባ ላይ አጋርነታቸውን ያሳዩ ወዳጅ ሀገራት በታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው መሆኑን በጎንደርና ደባርቅ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ምሁራን ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የህግ እና ፖለቲካ ሳይንስ ምሁራኑ እንደተናገሩት፤ በምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ተደጋጋሚ አጀንዳ እየቀረበ ያለው ተላላኪ መንግስት ለመመስረት የሚደረግ ሴራ ነው። 

በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁሩ አቶ መኳንንት ዱቤ፤ አንዳንድ አገሮች አሸባሪው ህወሃት ሽንፈት ሲከናነብና ሊጠፋ ሲቃረብ በፀጥታውን ምክር ቤት በኩል ጫና ለማሳደር ሙከራ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

ከዚህ ባለፈም 'ማዕቀብ እጥላለሁ' የሚል ማስፈራሪያ እንደሚታከልበትም ተናግረዋል።

በምክር ቤቱ መርህ ላይ ተመስርተው አቋም የያዙ ሀገራት መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ቻይና፣ ራሽያና ህንድ የመሳሳሉት አለም አቀፍ ህግን ተከትለው ገለልተኛ ሆነው ከኢትዮጵያ እውነት ጎን መቆማቸውን አውስተዋል።

ይህም ወዳጅነታቸው በታሪክ ትልቅ ስፍራ ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ ገልጸዋል።

የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁሩ  ስለሺ ዋለልኝ በበኩላቸው በአፍጋኒስታን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያና የመን የደረሰው ቀውስ በኢትዮጵያም እንዲደገም ፍላጎት ያላቸው አካላት መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ድርጊታቸውም ለአሸባው ህወሃት ድጋፍ በማድረግ እየተገለጠ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

"ሱዳን ኢትዮጵያን በመውረር መሬቷን  በሃይል ስትይዝ አንድም ቀን ተሰብስቦ የማያውቀው የፀጥታው ምክር ቤት በሰብአዊ መብት ስም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ለመፈትፈት የሚደረገው ጫና አሳፋሪ ነው" ብለዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ረዳት ፕሮፌሰር አንዳርጋቸው ተስፋሁን በበኩላቸው፤ ስትራቴጂካዊ በሆነው ምስራቅ አፍሪካ ላይ ታዛዥ መንግስታትን የመመስረት ፍላጎት መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ረገድ በስልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎታቸውን የሚያስፈጽም ሆኖ ስላላገኙት ተላላኪውን የህወሃት አሸባሪ ቡድን ዳግም ወደ ስልጣን ለመመለስ እየተረባረቡ እንደሚገኙ ነው ያመለከቱት፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና መበርታቱን ገልጸው፤ በዚህ ፈታኝ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም አጋርነታቸውን ያሳዩ ወዳጅ አገሮች ምስጋና ሊቸራቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም