የደቡብ ክልል ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከ2 ሺህ 600 በላይ የእርድ እንስሳትና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ክልል ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከ2 ሺህ 600 በላይ የእርድ እንስሳትና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ነሃሴ 21/2013(ኢዜአ) የደቡብ ክልል ለአገር መከላከያ ሰራዊት ለሶስተኛ ጊዜ ከ2 ሺህ 600 በላይ የእርድ እንስሳትና 200 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ፤ ድጋፉን ለአገር መከላከያ ሰራዊት አስረክበዋል።
በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክትም አሸባሪ ሃይሎችን በመመከት ለአገር ሉአላዊነት መከበር ለቆመው ሰራዊት ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በክልሉ በኩል ከዚህ ቀደም በደምሩ 113 ሚሊዮን ብር ለሰራዊቱ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው አሁን ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ 200 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገናል ብለዋል።
በዛሬው እለት 2 ሺህ 87 ሰንጋ እንዲሁም 580 ፍየልና በጎች ለሰራዊቱ ማስረከባቸውን ጠቅሰዋል።
ለአገር ህልውና ዘመቻው ክልሉ በቀጣይም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የአገር መከላከያ ሰራዊት የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋደር ጀነራል አስራት አያለው፤ ክልሉ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ አሸባሪውን ህወሃት በመመከት ለአገሩ የህልውና ዘመቻ እያሳየ ያለው ድጋፍና ተነሳሽነት ለሰራዊቱ ትልቅ የሞራል ስንቅ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የአሸባሪው ህወሃት አገር የማፍረስ እንቅስቃሴ ተቀልብሶ የቡድኑ እኩይ ድርጊት በአጭሩ ይቋጫል ሲሉም ተናግረዋል ብርጋደር ጀነራል አስራት።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያለው የህወሃት አሸባሪ ሃይል ጊዜ ሳይሰጠው መደምሰስ አለበት ብለዋል።
የክልሎች ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ተመስገን ቡርቃ፤ ህዝቡ ለራዊቱ እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ህልውና የማይደራደሩና ጠላትን ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን በተግባር ያሳዩበት አጋጣሚ መሆኑንም ጠቅሰዋል።