ቀጥታ፡

የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎቱ የአምቦ ነዋሪዎችን ስራ ያቀላጥፋል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ21/2013(ኢዜአ) በማዕከላዊ ምዕራብ ሪጅን ከተሞች የተጀመረው የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት ስራቸውን እንደሚያቀላጥፍላቸው የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

በአምቦ ከተማ በተደረገው የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች በየተሰማሩባቸው መስኮች ስራቸውን እንሚያሳልጥላቸው ነው የገለፁት።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምቦ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ኦብሰን ሞገስ እና በከተማዋ ከሚገኘው ኦሮሚያ ኅህብረት ስራ ባንክ የመጡት አቶ ደቻሳ መገርሳ፤ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎቱ መጀመር ለፋይናንስ ዘርፉ የላቀ ፋይዳ እንዳለው ነው የገለፁት፡፡ የካፌ እና ሬስቶራንት ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዳዊት ካሳሁንም የንግድ ስራቸውን ለማቀላጠፍና ደንበኞቻችውን በተሻለ ለማገልገል እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።

በአምቦ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት መጀመር መደሰቱን የገለጸው በሱፐርማርኬት ንግድ የተሰማራው ወጣት ሀሰን መሀመድም በተለይ ቴሌ ብር ስራችንን አቀላጥፎልናል ብሏል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አጃማ ቶሎሳ በበኩላቸው ኮቪድ-19 ስጋት በሆነበት ወቅት በከተማዋ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት መጀመሩ የወረርሽኙን ተጋላጭነትን በመቀነስ ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ በ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አገልግሎቱ አምቦን ጨምሮ አምስት ከተሞችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የአገልግሎቱ መጀመር የነዋሪዎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማሳደግ በዘለለ አስተማማኝ የዳታ አገልግሎት በመስጠት የደንበኞችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንደሚረዳ ነው የጠቆሙት፡፡

በማዕከላዊ ምዕራብ ሪጅን 334 ሺህ ደንበኞች የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድን አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ፤ 125 ሺህ ደንበኞችም የዳታ ተጠቃሚ ስለመሆናቸው ተነግሯል።

በሪጅኑ ከሚገኙ ደንበኞች 30 በመቶዎቹ የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች እንደሆኑ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ጠቁመዋል።

ከአገር አቀፍ የኢትዮ-ቴሌኮም ደንበኞች 42 በመቶ፣ በዓለም ከሚገኙ ደግሞ 68 በመቶዎቹ ስማርት ስልኮችን ይጠቀማሉ።

ኢትዮ-ቴሌኮም 56 ነጥብ 2 ሚሊዮን የደረሰውን የደንበኞቹን ቁጥር ወደ 64 ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ እየሰራም ነው።

ኩባንያው በቀጣይ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት የማስፋፊያ ስራዎችን በማጠናቀቅ በተለያዩ የክልል ከተሞች አገልግሎቱን በቅርቡ ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም