ቀጥታ፡

የአሸባሪው ህወሃት ርዝራዦች በክልሉ ችግር እንዳይፈጥሩ በቅንጅት እየተሠራ ነው

አሶሳ፤ ነሐሴ 21 / 2013 (ኢዜአ) የአሻባሪው ህወሃት ርዝራዦች ወደ ክልሉ እንዳይገቡና ችግር እንዳይፈጥሩ የስጋት ቀጣናዎች በመለየት በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቡድኑ  ርዝራዦች ሃገርን ለማፍረስ ዋነኛ መጠቀሚያ ያደረጉት ከትግራይ ቀጥሎ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ሙሳ ሃሚድ ለኢዜአ እንዳሉት ፤ክልሉ ከአጎራባች ሱዳን ጋር ይዋሰናል፤ የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎች ይህን ድንበር አቋርጠው ለመግባት በተደጋጋሚ ይሞክራሉ፡፡

በቅርቡ በክልሉ በኩል ድንበር አቋርጠው ሊገቡ እና ሊወጡ ሲሉ በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር የዋሉ  የጥፋት ቡድኑ ተላላኪዎች አስታውሰዋል፡፡

የአሸባሪው ህወሃት ርዝራዥ ዘራፊ ቡድን ከዚህ ቀደም በክልሉ በኢንቨስትመንት ሽፋን ከፍተኛ ሃብት እና ገንዘብ መዘረፉን ጠቁመው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለጥፋት የሚጠቀመው የገንዘብ ምንጭ ይኸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ይህ እንዳይቀጥል በክልሉ የሚገኙ የህወሃትን የገቢ ምንጮች ተለይተው የማዳከም ስራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በጠረፋማ አካባቢዎች ዋነኛ የስጋት ቀጣናዎች ተለይተው ህብረተሰቡን ያሳተፈ የተጠናከረ ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን ነው አቶ ሙሳ ያመለከቱት፡፡

አሸባሪው ቡድን  ክልሉን ተጠቅሞ ሃገር ለማፍረስ የሚያደረገውን ጥረት በሚመጥን ልክ የጥፋት እቅዱን የሚመክት ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

የጥፋት ቡድኑ በክልሉ ላይ ትኩረት ያደረገበት ዋነኛ ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ወደ ፍጻሜ እያደረሱ የሚገኘውን የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ማደናቀፍ እንደሆነ አቶ ሙሳ ገልጸዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ የጥፋት እቅዱን ለማስፈጸም  ከጉሙዝ ታጣቂ በተጨማሪ በህጋዊነት የተመዘገበ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጭምር እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ መንግስት እና ህዝብ የመተከል ዞን ሠላም ለማስጠበቅ ከአካባቢው ኮማንድ ፖስት ጋር በመቀናጀት  የሚደረገው ጥረት መኖሩንም ጠቅሰዋል፡፡

የሲዳማ፣ ደቡብ፣ ጋምቤላ እና ሌሎች ክልሎች ልዩ ሃይሎች በስፍራው ተሰማርተው እየከፈሉ የሚገኘውን መስዋዕትነት አቶ ሙሳ አመላክተዋል፡፡

በቢሮው የሚሊሻ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ደርጉ ሲያዳ በበኩላቸው፤ የሽብር ቡድኑን የጥፋት ሴራ ለማክሸፍ  በክልሉ ሶስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ለህብረተሰቡ ቅርብ የሆኑ የሚኒሻ አባላትን በስልጠና እና ትጥቅ ተጠናክረው የአካባቢያቸውን ደህንነት እንዲያስከብሩ መደረጉን ይናገራሉ፡፡

የክልሉ ህዝብም ከሚሊሻ አባላት ጋር  በመቀናጀት አካባቢውን ከሽብርተኛው ህወሃት ርዝራዦች እና ተላላኪው ሸኔ እየጠበቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም የሚሊሻ አባላት ማሳ በማረስና መኖሪያ ቤታቸውን በመጠገን ለቤተሰቦቻው እንክብካቤ እያደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

የመንግስት ሠራተኛውም ከወር ደመወዛቸው ተቆራጭ በማድረግ ሚሊሻውን እየደገፈ እንደሚገኝ አቶ ደርጉ ጠቁመዋል፡፡

ሃገራችን ከአሸባሪው የህወሃት  የጥፋት ቡድን ለመጠበቅ  ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተን እየሠራን ነው ያሉት ደግሞ  የሚሊሻ ምክትል ጋንታ መሪ አልባቡ አዲሱ ናቸው፡፡

የህብረተሰቡን ሠላም ለመጠበቅ ባለን አቅም ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ነው ያሉት።

ኮማንደር የኑስ ኡስማን በበኩላቸው፤ ሚሊሻው ከልዩ ሃይል ጋር መረጃ ከመለዋወጥ ጀምሮ በተለይም የአሸባሪው ህወሃት ርዝራዦች ቡድን ወደ ክልሉ ሰርገው እንዳይገቡ አካባቢአችንን ነቅተን እየጠበቅን ነው ብለዋል፡፡

የጥፋት ቡድኑ ተላላኪዎች ሊገቡ የሚችሉባቸውን አካባቢዎችን በሚገባ ለይተን እናውቃለን የሚሉት ኮማንደሩ በተለይም የክልሉ ጠረፍ አካባቢ ደግሞ ዋነኛ ትኩረታቸው መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡

የሃገራችን ሠላም ወደ ቀደመ ሁኔታ እስኪመለስ የማንከፍለው መስዋዕትነት የለም ብለዋል ኮማንደር የኑስ ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም