ቀጥታ፡

የቡና አምራቹን አርሶ አደር ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የግብይት አማራጮች ተዘርግተዋል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 21/2013 (ኢዜአ) የቡና አምራች አርሶ አደሮችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የግብይት አማራጮች መዘርጋታቸውን የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን ገለጹ።

በሁለተኛው ዙር ዓለምአቀፍ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር 40 አይነት የቡና ዝርያዎች የቀረቡ ሲሆን 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።


የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በሁለተኛው ዙር ዓለምአቀፋ ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር ላሸነፉ አርሶ አደሮች እውቅናና የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል።


በሽልማት መርሃ ግብሩ ላይ የታደሙት የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን ኢትዮጵያ ካላት ቡና የማምረት ሰፊ አቅም ልክ እየተጠቀመች እንዳልሆነ ተናግረዋል።


ይህንን ለማስተካከልም እስከታችኛው የቡና ሰንሰለት ድረስ በመውረድ የድጋፍና ክትትል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።


ከስራዎቹ መካከል ቡና አምራቹ አርሶአደር የግብይት አማራጮች እንዲሰፉለት በማድረግ ምርቱን ያዋጣኛል በሚለው ዋጋ እንዲሸጥ የሚያስችሉ አማራጮች መቀመጣቸውን ጠቅሰዋል።


የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር መካሄዱ አርሶ አደሩ ቀጣይ የገበያ ትስስር እንዲኖረውና የዋጋ ተወዳዳሪነቱን በማጎልበት የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሳደግ ዕድሎች እየከፈተ መሆኑንም አክለዋል።


ሚኒስትሩ አርሶ አደሩ ጥራቱን የጠበቀ ቡና በማምረት ተጠቃሚነቱ እንዲያድግ የበለጠ መትጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል።


የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው መንግስት በአገሪቷ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አንስተዋል።


በተለይም ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ ድርሻ ያለው የቡና ምርት እድገት እንዲያስመዘግብ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


የቡና ምርት ተዋናዮችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድም በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።


በዚህ ረገድ ለአርሶ አደሩ እየተሰጠ ያለው እውቅና በቡና ምርቱ ዕድገት ላይ ተነሳሽነት እየፈጠረ መሆኑን ነው የገለጹት።


ባለስልጣኑ ለቡና አምራቹ የሰጠው እውቅናም የአርሶ አደሩ ድካም እውቅና እንዲያገኝ ለማድረግ በማለም እንደሆነ ተናግረዋል።


በተጠናቀቀው የ2013 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 927 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን በ2014 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም