በአገር ህልውና ዘመቻው የምሁራን ሚና ምን ይሁን? - ኢዜአ አማርኛ
በአገር ህልውና ዘመቻው የምሁራን ሚና ምን ይሁን?
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2013(ኢዜአ)የኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታን አስመልክቶ በውስጣዊና ውጫዊ ጠላት ጫና ለመፍጠር የሚደረገውን ሙከራ ለመመከት በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ለአገራቸው ዲፕሎማት በመሆን በተሻለ ደረጃ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ተገለጸ።
በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ የምሁራንን ሚና በሚመለከት የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
በመድረኩ ላይ ተሳተፊ ከነበሩት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሠብለወርቅ መኮነን፤ የኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ በውስጣዊና ውጫዊ ጠላት ጫና ውስጥ የገባችበት፣ ብቻዋን የቆመችበት አሳሳቢ ወቅት ነው ብለዋል።
ይህንን ለመመከት በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን አሁን ላይ በተሻለ ደረጃ ለአገራቸው ዲፕሎማት በመሆን እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል።
ሆኖም በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ምሁራን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የጋራ ትብብር ፈጥረው ለአገራቸው ዘብ የሚቆሙበት "የቁርጥ ቀን ጊዜው አሁን ነው" ብለዋል ዶክተር ሠብለወርቅ።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኬሚካል ምህንድስና መምህርና የልዕቀት ማዕከል ዲን ዶክተር አለሙ ጎንፋ፤ የውጭ ሃይሎች ኢትዮጵያን ለመከፋፈል በብዙ ቢራመዱም በህዝብ አንድነት መክሸፉን ይናገራሉ።
ከኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ አቀማምጥና ከታሪኳ ተነስተው ወደ ፊት ሃያል እንዳትሆን በእንጭጩ መቅጨት የሚፈልጉ የሩቅና የቅርብ ጠላቶች እንዳሉም አስረድተዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያን ከገጠማት ወቅታዊ ፈተና ለማስወጣት በተለይም የምሁራን ተሳትፎና ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ምሁራን ሳይንሳዊ በሆነ፣ የአገር አንድነትን ታሳቢ ባደረገና ከስሜታዊነት በራቀ አግባብ በአንድነት ቆመው መከላከያን ማገዝ፣ ማህበረሰቡን የማስተባበር ተግባራትን በስፋት ማከናወን አለባቸው ነው ያሉት ዶክተር አለሙ።
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ልማትና ምህድስና ምሁሩ ዶክተር ዳንኤል ሊሬቦ "ወቅቱ ሁላችንም ለኢትዮጵያ በጋራ የምንቆምበት ወሳኝ ጊዜ ነው" ይላሉ።
በአገር ግንባታ ሂደት ምሁራን በዕውቀታቸው አገራዊ መፍትሄ በማፍለቅ፣ በጥናትና ማማከር፣ ህዝብ በማንቃት ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በዲፕሎማሲና በሚዲያ መረጃ በመስጠት የነቃ ተሳትፎ ማድረግና የውስጥና የውጭ ጠላቶችን ታግሎ ለማሸነፍ ግንባር ቀደም ሊሆኑ ይገባልም ነው ያሉት።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን ነዋይ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የገጠማት ጦርነት ከአንድ ቡድን ጋር ብቻ ሳይሆን "ዓለም አቀፍ ድባብ ያለው ነው" ብለዋል።
በኢኮኖሚ አሻጥርና ጫና፣ በመረጃ ልውጥ፣ በዲፕሎማሲው ጦርነት ጥንቃቄ አድርጎ መራመድና መታገልም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ከገባችበት ወቅታዊ ችገር እንድትወጣ፣ ምን አይነት ፖሊሲ መንደፍ እንዳለባትና ወደ ተረጋጋ ሁኔታ መመለስ በምትችልበት ሁኔታ ላይ የምሁራን ተሳትፎ ይጠይቃል ነው ያሉት ዶክተር ሰለሞን።