የማዕድን ምርቶች ወደ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ በቅንጅት መሰራት አስፈላጊ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማዕድን ምርቶች ወደ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ በቅንጅት መሰራት አስፈላጊ ነው
ነሐሴ 21/2013 (ኢዜአ) የማዕድን ምርቶች ወደ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ በቅንጅት መሰራት ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ መሆኑ ተገለፀ፡፡
በዛሬው ዕለትም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽኖች እና የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በሰላምና በማዕድን ምርት ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን በጋራ መግታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አካሂደዋል፡፡
የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ በምክክር መድረኩ ላይ ባሰሙት ንግግር ከግብርና ቀጥሎ የሀገራችን የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የማዕድን ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን መቅረፍ ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ከፀጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት ሰላም በማረጋገጥም በማዕድን ምርትና ለገበያ የማቅረብ ሂደቱን የተሳለጠ ለማድረግ ሰላም አስፈላጊ ነው፡፡
ከሰላሙም በተጨማሪም በምርቱና በግብይት ሰንሰለቱ ላይ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን መፍታትም ችላ የሚባለው ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ፍቃድ የተሰጣቸው ግለሰቦችና ተቋማት በተሰጣቸው የአምራችነትና የአዘዋዋሪነት ፍቃድ መሰረት ህጋዊ ስርዓት ተከትለው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ፍቃድ የወሰዱት አካላት ያመረቱትን ወርቅ በየወሩ ወደ ባንክ ገቢ ለማድረግ በገቡት ውል መሰረት እየሰሩ መሆናቸውን በመከታተል የአሻጥር ድርጊት እንዳይፈፀምባቸው መጠነ ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይ አምራቾችንና የወርቅ ምርቱን በህጋዊ የግብይት ሰንሰለት ወደ ባንክ ለማቅረብ ፍቃድ የወሰዱ አዘዋዋሪዎችን የመደገፍና የማበረታታት ስራዎችን እንሰራለን ያሉት ኢንጂነር ታከለ ኡማ ግለሰቦችም ሆነ ተቋማት በገቡት ውል መሰረት መስራታቸውንና የወርቅ ምርትን ወደ ባንክ ማምጣታቸውን በየወሩ በመገምገም የማስተካከያ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው የፀጥታ ስራዎችን በማጠናከር ሀገራችን ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ወደ ኋላ ለመቀልበስ የሚደረገውን ሙከራ በጋራ መከላከል ይገባናል፡፡
ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የምክክር መድረኩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም ገልፀዋል ፡፡
በግልም ሆነ በቡድን ደረጃ በወርቅ ግብይት ላይ ችግር እየፈጠሩ ያሉ አካላትን የፌደራል ፖሊስና ማዕድኑ የሚወጣባቸው ክልሎች ላይ ያሉ የፖሊስ አመራሮች ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ጋር በመቀናጀት የጥበቃ ስራዎችን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራ ኮሚሽነር ጄነራሉ በአፅኖት ገልፀዋል፡፡