ቀጥታ፡

አሸባሪው እስኪደመሰስ ድረስ ለሠራዊቱ ስንቅ በማዘጋጀት የደጀንነት ሚናችን እናጠናክራለን

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 21/2013 (ኢዜአ)  አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሙሉ በሙሉ እስኪደመሰስ ድረስ ለሠራዊቱ ስንቅ በማዘጋጀት የደጀንነት ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የባህር ዳር ከተማ ሴቶች ገለጹ።

በከተማ አስተዳደሩ በተደረገ ሃብት የማሰባሰብ እንቅስቃሴ እስካሁን ከ118 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት ማሰባሰብ እንደተቻለ ተመላክቷል።

በጣና ክፍለ ከተማ ሽምብጥ ቀበሌ በስንቅ ዝግጀት ላይ የነበሩት ወይዘሮ የህዝቡጥላ ካሳ ኢትዮጵያ በአሽባሪውና ወራሪው ኃይል ሰላም ማጣቷን ገልጸዋል።

የሀገርንና የህዝብን ደህንነት ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ለመታደግ ወደ ግንባር ለዘመተው መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሺያና ፋኖ ስንቅ በማዘጋጀት አጋርነታቸውን እያሳዩ መሆኑንም ተናግረዋል።

"ህወሓት ሀገሪቱን ለመበተን በሃገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ አጋሮቹን አስተባብሮ እየሰራ ቢሆንም ሀገራችንን ለመታደግ በጋራ ተነስተናል፤ የደጀንነት ሚናችንንም እናጠናክራለን" ብለዋል።

የፋሲሎ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 01 ነዋሪ ወይዘሮ አመለወርቅ አለነ በበኩላቸው ህወሓትና አጋሮቹን ለመደምሰስ በግንባር ለተሰለፈው ሠራዊት የሚደረገው ድጋፍ እንደሚጠናከር ተናግረዋል።

እርሳቸውን ጨምሮ ታዳጊዎች፣ ወጣት ሴቶች፣ እናቶችና አዛውንቶች ሳይቀር በስንቅ ዝግጅቱ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።

"በግንባር ለሚገኘው ሠራዊት ስንቅ አዘጋጅቶ መላክ ትንሹ መስዋዕትነት ነው" ያሉት ወይዘሮዋ፤ ሁሉም ነገር የሚደምቀው በሀገርና ሰላም ሲኖር ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

"ሰላም ከታጣ ልጅ ወልዶ መሳም፣ ወጥቶ መግባትና ሰርቶ መለወጥ እንደማይቻል በመገንዘብ ለሠራዊቱ የጀመርነውን የኋላ ደጀንነት ልናጠናክር ይገባል" ብለዋል።

የህወሓት የጥፋት ቡድን በወረራ ከያዛቸው የአማራና አፋር አካባቢዎች ለቆ እስኪወጣና ግብዓተ መሬቱ እስኪፈጸም ድረስ ትግላቸውን አጠናክረው ለመቀጠል መዘጋጀታቸውንም ወይዘሮ አመለወርቅ አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም በግንባር እየተዋደቀ ላለው የፀጥታ ኃይል ዳቦ ቆሎና ደረቅ እንጀራ አዘጋጅተው መላካቸውን የገለፁት ደግሞ የዚሁ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሃይማኖት አዲሱ ናቸው።

አሁንም በበሶ እና ቆሎ ዝግጅት ሥራ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ህብረተሰቡ ያለው በገንዘቡ፣ የሌለው በሃሳብና በጉልበቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የህልውና ዘመቻ የሎጂስቲክስና ሃብት አሰባሰብ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አላዩ መኮንን የህልውና ዘመቻውን ተከትሎ የስንቅ ዝግጅትና ገንዘብ የማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

"እስካሁንም የመንግስት ሠራተኛውን ጨምሮ ከነጋዴውና ከብረተሰቡ በጥሬ ገንዘብ ከ118 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት ማሰባሰብ ተችሏል" ብለዋል።

በማህበረሰቡ ደረቅ ምግቦችን በማዘጋጀት ለሠራዊቱ የማቅረብ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው፣ እስከዛሬም 2 ሺህ 161 ኩንታል ደረቅ ሬሽን፣ በሶና ቆሎ ተዘጋጅቶ መላኩን አመልክተዋል።

"በቅርቡ የስንቅ ዝግጅቱን ህዝባዊ ማድረግ በመቻሉ በየቀበሌው የስንቅ ዝግጀት ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል" ብለዋል።

በቀጣይም የህወሓት የጥፋት ቡድን ከወረራቸው አካባቢዎች ተደምስሶ እንኪያልቅ ድረስ የደጀንነት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የህልውና ዘመቻ በስኬት እስኪጠናቀቅ ድረስም ወጣቱ አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች ለመጠበቅ ተቀናጅቶ የጀመረውን ሥራ እንዲያጠናክርም አቶ አላዩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም