የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመረጃ አያያዝና አደረጃጀት ሥርዓት ሊሻሻል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመረጃ አያያዝና አደረጃጀት ሥርዓት ሊሻሻል ይገባል
ነሀሴ 21/2013 (ኢዜአ) የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመረጃ አያያዝና አደረጃጀት ሥርዓታቸውን ማሻሻል እንደሚገባቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ።
ሚኒስቴሩ በተቋማት መስረታዊ መረጃ አያያዝና በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ላይ ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለቤቶች ጋር እየመከረ ነው።
በምክክሩ ላይ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የመረጃ አያያዝና አደረጃጀት ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው ሚኒስቴር ዴኤታው ዶክተር ሙሉ ነጋ ገልፀዋል።
ይሁንና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመረጃ አያያዝና አደረጃጀት ተግባር ሰፊ ክፍተት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ይህንን ክፍተት በመሙላት ትክክለኛ መረጃ ማደራጀት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰው ኃይል ከማፍራት፣ ከማኀበረሰብ አገልግሎትና ከምርምር ተቋምነታቸው ባሻገር አገራዊና ማኅበራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በአገራዊ ጉዳዮችና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተሳትፏቸውን ማጎልበት እንደሚኖርባቸውም ተናግረዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ያነሱት ዶክተር ሙሉ፤ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች፣ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን እንዲደግፉ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም የአገርን ሕልውና ለማስጠበቅ ለሚተጋውን የመከላከያ ሠራዊት ድጋፋቸውን በማሳየት አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።