ቀጥታ፡

ሽብርተኞች ተደምስሰው ዘላቂ ሰላም እስኪረጋገጥ ለመከላከያ ሠራዊት የምናደርገው ድጋፍ አይቋረጥም

ዲላ፤ ነሐሴ 20 ቀን 2013(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት ተደምስሶ የመጨረሻውን የድል ብስራት እስክንሰማ ለመከላከያ ሠራዊት የምናደርገው ድጋፍ አይቋረጥም አሉ የጌዴኦ ዞን ነዋሪዎች።

ነዋሪዎቹ ዛሬ በካሄዱት ሰልፍም ያሉትን ከመፈጸም ወደኋላ አላሉም። ለሦስተኛ ጊዜ ባደረጉት ድጋፍ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ አድርገው በተግባር አሳዩ።

ወይዘሮ ፍሬዘር ተገኝ የሰልፉ ተሳታፊ ናቸው። “አሸባሪው ቡድን የኢትዮጵያ ነቀርሳ በመሆኑ ተነቅሎ እንዲጠፋ አገራዊ ግዴታቸዬን እየተወጣሁ ነው” ብለዋል።

በገንዘብና በዓይነት የሚያደርጉትን ድጋፍ ከማጠናከር ባለፈ በግንባር እንደሚሰለፉና ለዚህም በፈቃደኝነት ወታደራዊ ስልጠና እየተከታተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሃት ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሞ የመጨረሻውን የድል ብስራት እስክንሰማ ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፋችን አይቋረጥም ሲሉ ለኢዜአ ዘጋቢ ነግረውታል።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ኢትዮጵያ አዱኛ በበኩላቸው ህጻናትንና ሴቶችን በግፍ የሚጨፈጭፈው አሸባሪ ቡድን ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ሊያወግዘው ይገባል ብለዋል።

ሆኖም ኢትዮጵያውያን ወራሪውና ዘራፊው ቡድን ተደምስሶ ሙሉ ለሙሉ ፊታችንን ወደ ልማት እስክናዞር ለመከላከያ ሰራዊት የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ተስፋጽዮን ዳካ በበኩላቸው ''የአገር ሉአላዊነት መደፈር ያስቆጣን ኢትዮጵያዊያን ከጫፍ ጫፍ በአንድ ድምጽ መነሳታችን በውስጥም በውጭም ላሉ ጠላቶች ፈተና ሆኖባቸዋል'' ይላሉ።

''በአገራችን የተጋረጠውን ፈተና ለመቀልበስ ለመከላከያ ሰራዊት ያለንን አጋርነት በማሳየት ከጎኑ መቆም ይገባናል'' ሲሉም አስረድተዋል።

የዞኑ ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ስንቅ ከማዘጋጀት ጨምሮ ደም በመለገስ አጋርነታቸውን ሲያሳዩ መቆየታቸውን የተናገሩት የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ወይዘሮ ለምለም ከበደ ናቸው።

የዞኑ ሕዝብ ዛሬም ለሶስተኛ ጊዜ 22 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ እንዲሁም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ 80 ስንጋዎች፣ 66 በጎችና ፍየሎች ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

''ድጋፉ ህወሃት ተደምስሶ የመጨረሻውን የድል ብስራት እስክንሰማ አይቋረጥም''ብለዋል ምክትል አስተዳዳሪዋ። 

በሐሰት ፕሮፓጋንዳና በኢኮኖሚ አሻጥር የተከፈተብንን ጦርነት በጋራ መመከት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

አሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ በተወገዙበት በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የጌዴኦ ዞን የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተካፍለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም