ሀገርን የማዳኑ ዘመቻው እንዲሳካ በሁሉም መስክ ድጋፋችን ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገርን የማዳኑ ዘመቻው እንዲሳካ በሁሉም መስክ ድጋፋችን ይጠናከራል
ድሬዳዋ ፤ ነሐሴ 20/2013(ኢዜአ) ሽብርተኞቹን ህወሓትና ሸኔን ለማጥፋት የተጀመረው ዘመቻ በድል እንዲጠናቀቅ በሁሉም መስክ ድጋፋቸውን እናጠናክራለን ሲሉ የድሬዳዋ ገጠር ክላስተር ነዋሪዎች ተናገሩ።
በአራት ክላስተር የሚገኙ 38 የገጠር ቀበሌዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ መሳካት ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ የለገሱት ከ2 ሚሊዮን 208 ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያላቸው 25 በሬዎችን፣ 85 የፍየል ሙክቶች እና ሁለት ግመሎችን ድጋፍ አድርገዋል።
ሠራተኞችና ሌሎችም ነዋሪዎች 828ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ አበርክተዋል፡፡
የዋሂል ገጠር ክላስተር ቀበሌዎች አስተባባሪ አቶ ሁሶ ሐሰን ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ በቅርቡ ጋብቻ የፈጠሩት አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ የተሰማሩበት ሀገር የማፍረስ ተግባር በተባበረ ክንድ ይከሽፋል፡፡
"የገጠሩ ነዋሪዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ለሀገር ደህንነት እየከፈሉት ያለው መስዋዕትነት በድል እንዲጠናቀቅም የጀመሩት ድጋፍ ይጠናከራል" ብለዋል፡፡
"ሸኔ የኦሮሞን ህዝብ ሲገድልና ሲያሳድድ ከነበረ የህወሓት ሽብርተኛ ቡድን ጋር ተቀናጅቶ ሀገር ለመበጥበጥ የጀመረውን እኩይ ተግባር በፅናት እንቃወማለን" ያለው ደግሞ ወጣት አርሶ አደር አብደላ አህመድ ነው፡፡
ወጣቱ እንዳለው ፤ ህወሓትና ሸኔን ለማስወገድ እየተካሄደ ያለው የህግ ማስከበር ዘመቻ እንዲሳካ የገጠር ወጣቶች ግንባር ድረስ መዝመት ጀምረዋል።
ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የአካባቢያቸውን ሠላምና ልማት እየጠበቁ ያሉ ወጣቶችም መኖራቸውን ነው የገለጹት።
የጀሎበሊና ገጠር ቀበሌ አርብቶ አደር አብዲ ራቢ በበኩላቸው "ሀገርን ለማዳን ህይወታቸውን እየሰጡ ላሉ የአገር መከላከያ ሠራዊት የሚደረገው ድጋፍ እስከመጨረሻው ይቀጥላል" ብለዋል፡፡
"ሀገር ከሌለ ምንም ነገር የለም፤ ሀገር ለማዳን የተጀመረው ዘመቻ እንዲሳካ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን" ሲሉም አክለዋል፡፡
"ሀገርን ለማዳን በግንባር ለተሰለፉ ጀግኖቻችን ስንቅ ማዘጋጀቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ያሉት ደግሞ የሴት አርሶ አደር ደሃብ ሃሰን ናቸው፡፡
የገጠር ሴቶች አካላዊ ጥንካሬ ግንባር ድረስ በመሄድ ሠራዊቱን ለማገልገል አስተማማኝ በመሆኑ ሁኔታዎች እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡
ዛሬ በተካሄደው የድጋፍ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ የአስተዳደሩ ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴሰብሳቢ አቶ ከድርጁሃር ህዝቡ በሚችለው ሁሉ ሀገሩን ከጥፋት ለማዳን ህብረቱን አጠናክሮ በአንድነት እየተረባረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
"የዚህ አንዱ ማሳያ ዛሬ የገጠር ክላስተሮች ለሠራዊቱ ያበረከቱት ድጋፍ ነው፤ ላደረጉትም እገዛ አስተዳደሩ ምስጋናውን ያቀርባል" ብለዋል፡፡
"በደጀንነት የምናደርገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴም ሆነ በአውደ ግንባር ተሰልፈን የምናካሄደው ጦርነት አገርን የማዳን ፍትሃዊ ጦርነት መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል" ብለዋል አቶ ከድር ፡፡
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል የድሬዳዋና የሐረሪ ክልል ላይዘን ጽህፈት ቤት አዛዥ ኮሎኔል ዮናስ ሮባ "የህዝቡ ድጋፍ የተጀመረው ሀገር የማዳን ተልዕኮ ፈጣንና ስኬታማ ያደርገዋል" ብለዋል፡፡
"ሀገር አፍራሹ ህወሓት ጉድጓድ መግባት ይችልበታል፤ እኛ ደግሞ ከጉድጓድ አውጥተን መቅበር እንችላለን" ብለዋል፡፡