ቀጥታ፡

ከአሸባሪ ቡድኑ ጋር የሚጠየቅ ድርድር ኢትዮጵያን ለማዳከምና ጊዜ ለመግዛት የታቀደ ሴራ ነው

ነሐሴ 20/2013 (ኢዜኣ) ከአሸባሪ ቡድኑ ጋር ድርድር የሚጠየቅ ድርድር ኢትዮጵያን ለማዳከምና ጊዜ ለመግዛት የታቀደ ሴራ ነው ሲሉ ምሁራን ተናገሩ።
በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ የሚመክር የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ያሳተፈ አገር አቀፍ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከአሸባሪው ቡድን ጋር መደራደር እንዳለበት በተለያዩ የውጭ ኃይሎች  በሚንጸባረቀው ሃሳብ ላይ ኢዜአ የመድረኩን ተሳታፊ ምሁራን አነጋግሯል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሠብለወርቅ መኮነን፤ አሸባሪ ቡድኑ መከላከያ ሰራዊቱን ከማጥቃቱ ቀደም ብሎ በርካታ ሽምግልና ተሞክሮ ቡድኑ የቀረበለትን ድርድር አሻፈረኝ ብሎ መግፋቱን ያወሳሉ።

''መከላከያን መምታት ማለት የአገር ክህደት ነው" ያሉት ዶክተር ሠብለወርቅ መከላኪያ ሰራዊቱ በተኛበት ከተወጋ በኋላ ድርድር አይታሰብም'' ባይ ናቸው።

ይህ ቡድን ኢትዮጵያን ለማጥፋት ቆርጦ ተነስቷል የሚሉት ዶክተር ሠብለወርቅ አሁን ላይ ድርድር ማለት ኢትዮጵያን ለማዳከምና ጊዜ ለመግዛት የታለመ ሰበብ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይልቁንም አገር ለማጥፋት የተነሳውን የጥፋት ቡድን አጥፍቶ ህዝቡን በአንድነት ወደ ልማት የሚመጣበት፣ የትግራይ ህዝብም እፎይታ የሚያገኝበት ጊዜ መምጣት እንዳበት ጠቁመዋል።

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የልዕቀት ማዕከል ዲን ዶክተር አለሙ ጎንፋ፤ በአሸባሪነት የተፈረጀው ቡድን እየፈፀመ ያለው ተግባር ለእርቅና ለድርድር የሚያስቀርብ አንዳልሆነ ይናገራሉ።

''በአሸባሪነት ከተፈረጀ በኋላ በሌሎች ክልሎች እያካሄደ ያለው ጦርነት አሸባሪነቱን በተግባር የሚያረጋገጥ ነው፤ ከዚህ ቡድን ጋር የሚደረግ ድርድር መኖር የለበትም '' ብለዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ልማትና ምህድስና ምሁሩ ዶክተር ዳንኤል ሊሬቦ ከአሸባሪው ህወሃት ጦርነት ከመቀስቀሱ ቀደም ብሎ መንግስት ምሁራንን፣ የአገር ሽማግሌዎችንን ጨመሮ ሁሉንም የሰላም አማራጮች አሟጦ መጠቀሙን ያነሳሉ።

አሸባሪው ቡድን በቀሰቀሰው ጦርነት በርካቶች ተፈናቅለዋል፤ ተርበዋል፣ ቁሳዊ ኪሳራ ደርሷል በመሆኑም የጠፋውን ሁሉ ወደነበረበት ለመመለስ መንግስት የጀመረው የህግ ማስከበር ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያምናሉ።

ጦርነቱ ዓለም አቀፋዊ ጫና ያለብት በመሆኑ ብርቱ ጥንቃቄና ትብብር የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን ነዋይ ናቸው።

''ድርድር የሚያስፈልገው ከህጋዊ አካል ጋር እንጂ አገርን ከሚያፈርስ ቡድን ጋር መሆን እነደሌለበት ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም