የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ምሑራን በዲጂታል ዲፕሎማሲው ብርቱ ትግል ሊያደርጉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ምሑራን በዲጂታል ዲፕሎማሲው ብርቱ ትግል ሊያደርጉ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 20 ቀን 2013 (ኢዜአ) የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ምሑራን የአገር ሕልውናን ለማስጠበቅ በዲጂታል ዲፕሎማሲው መስክ ብርቱ ትግል ማድረግ እንዳለባቸው አንድ የዘርፉ ምሁር ገለጹ።
በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህርት ሕይወት ዮሐንስ እንደሚሉት ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ከባድ ትግል የሚጠይቅ ነው።
የጋዜጠኝነት ሙያ ከባድ ማህበራዊ ኃላፊነትን የሚጠይቅ፣ ለድምጽ አልባዎች ድምጽ እንደሆነ የዘርፉ ምሑራንና ሚዲያዎች ህብረተሰቡን በማንቃት፣ በአገር አንድነትና ሕልውና ትግል ጠንካራ ሥራ ይጠበቅባቸዋል።
ማህበራዊ ሚዲያ ወጣቱ በስሜትና ግብታዊነት እንዲወሰን ያደረገበት ሰዓት በመሆኑ፤ የሐሰት መረጃን በማጋለጥና በመመከት ረገድ የጋዜጠኝነትና ኮሙንኬሽን ምሑራን ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በዚህ ሰዓት ማንንም የመደገፍ ወይም የፖለቲካ መወገን ሳይሆን አገርን የማዳን ጉዳይ መሆኑን አንስተው፤ ጦርነቱ ከውጭ ኃይላት ጋር በመሆኑ ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻውን መታገል ተገቢ መሆኑን ነው ያነሱት።
በመሆኑም የዘርፉ ምሑራን ትልቅ መሳሪያ በሆነው የዲጂታል ዲፕሎማሲው ላይ በመሳተፍ አገርን የመታደግ እንቅስቃሴን ማገዝ ይገባቸዋል ብለዋል።
የውጭ ኃይሎች ቀዳዳ እየፈለጉ ኢትዮጵያን ከሚወጉበት ስልቶች አንዱ ዲጂታል ፕላትፎርም ወይም የመገናኛ ዘዴ መሆኑንም ያስረዳሉ።
ጋዜጠኝነትና ተግባቦት የራሱ የሆነ መርህና ስነ-ምግባር ቢኖረውም የትኛውም ሚዲያ ለአገር ጥቅምና ለአገሩ መንግሥት እንደሚወግን ይናገራሉ።
የምዕራባውያን ሚዲያዎችም በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ዘመቻ ከአገራቸው ጥቅም አንጻር በመወገን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ለማካሄድ እንጂ የኢትዮጵያ ችግር ከንክኗቸው እንዳልሆነ ገልጸዋል።
በመሆኑም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃንና የሚዲያ ምሑራን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለአገር መብትና ጥቅም ወግነው መሥራት ይገባቸዋል ነው ያሉት።
በሚዲያና ኮሙንኬሽን ዘርፍ ምሑራን የጋዜጠኞች በር እያንኳኩ ሐሳብ የሚጠይቋቸው ሳይሆን፤ የሚዲያውን በር እያንኳኩ ስለአገራቸው በዲጂታል ዲፕሎማሲው መስክ ሐሳብ ማጋራት አለባቸው ብለዋል።
የህወሃት አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍርስ ሲኦልም ቢሆን እንገባለን በማለት እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።