ቀጥታ፡

በአማራና ትግራይ ክልሎች የመቀንጨርን ችግር ለመቀነስ ተጨማሪ ስራዎች ያስፈልጋሉ

ነሐሴ 20/2013(ኢዜአ) በአማራና ትግራይ ክልሎች የመቀንጨርን ችግር ለመቀነስ ተጨማሪ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በመቀንጨር ችግር ምክንያት በየዓመቱ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እያጣች መሆኑም ተገልጿል።

ሁለተኛው ምዕራፍ የምግብና ስርዓተ ምግብ ስትራቴጂ እንዲሁም የሰቆጣ ቃል ኪዳን ማስፋፊያ ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ሆኗል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ እንዳሉት ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀና በንጥረ ነገር ይዘቱ የተሟላ ምግብ መመገብ ጤናማና አምራች እንዲሁም የፈጠራ ብቃት ያለው ዜጋ ለማፍራት ወሳኝ ነው።

በመጀመሪያው የሰቆጣ ሰነድ ትግበራ በሙከራ ደረጃ የተጀመረባቸው የትግራይና አማራ ክልሎች ውጤቶች ተገኝተዋልም ብለዋል።

በዚህም በአማራ ክልል በተተገበረባቸው ወረዳዎች የመቀንጨር ምጣኔው ከ51 በመቶ ወደ 43 በመቶ ዝቅ ያለ ሲሆን በትግራይ ክልል ደግሞ ከ39 በመቶ ወደ 32 በመቶ ቀንሷል።

በመሆኑም በአማራና ትግራይ ክልሎች የመቀንጨርን ችግር ለመቀነስ ተጨማሪ ስራዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል ዶክተር ሊያ።

መንግስት ምግብና ስርዓተ ምግብን ለማሻሻል ያከናወናቸው ስራዎች ውጤት ማስገኘታቸውንም ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።

ባለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ የመቀንጨር ምጣኔ 58 ወደ 37 በመቶ ዝቅ ያለ ሲሆን ከክብደት በታች ምጣኔው ደግሞ ከ41 ወደ 21 ቀንሷል።

ይሁንና አሁንም መቀንጨር የኢትዮጵያ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ሆኖ በመቀጠሉ ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ የስርዓተ ምግብ ችግር ዜጎችን ለህመምና ሞት ከመዳረጉ ባለፈ ለአገሪቷ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተግዳሮት ነው ብለዋል።

ችግሩን ለመቀነስ የሚደረግ ርብርብ የዜጎችን ጤንነትና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ ለአገሪቷ ምጣኔ ሃብት ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንዳለው በመግለጽ።

መንግስት ስርዓተ ምግብን ለማሻሻል የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነና ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል።

በ2000 ዓ.ም ብሔራዊ የስርዓተ ምግብ ፖሊሲና ስትራቴጂ መውጣቱን አስታውሰው ከዚህ ባለፈ የሰቆጣ ስምምነት ሰነድ ወደ ትግበራ መግባቱ የስርዓተ ምግብ ችግርን ለማቃለል የድርሻውን መወጣቱን ጠቁመዋል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ በአማራና ትግራይ ክልሎች መቀንጨርን ለመቀነስ የተሰሩትን ስራዎችም አድንቀዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የሰቆጣ ቃልኪዳን የማስፋፊያ ፕሮግራም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

"ስለማንኛውም አገራዊ ጉዳይ ስንነጋገር አገራችን ኢትዮጵያ በከፍተኛ ፈተና ውስጥ ያለች መሆኗን ለደቂቃ ዘንግተን አይደለም'' ያሉት ፕሬዚዳንቷ የስርዓተ ምግብ ችግር ባሉብን ችግሮች ላይ ሌላ እንዳይጨምርብን የበለጠ መጠንቀቅ የሁላችን ድርሻ  ነው ብለዋል።

ዜጎች የመኖር መብታቸው የሚረጋገጠው የአገር አንድነትና ሉዓላዊነት ሲከበር መሆኑንም አንስተዋል።

ለመርሃ ግብሩ የአፍሪካ ልማት ባንክ 48 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ድጋፍ ማድረጉንና መንግስትም 500 ቢሊዮን ብር መመደቡን ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።

ለአስር ዓመታት ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ለሚጠበቀው ሁለተኛ ምዕራፍ የምግብና ስርዓተ ምግብ ስትራቴጂ ከ111 ቢሊዮን ብር በላይ ይጠይቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም