''አሸባሪው የህወሃት ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች ጥቁር የታሪክ ጠባሳ ጥሏል''-የቢሮ ኃላፊዋ - ኢዜአ አማርኛ
''አሸባሪው የህወሃት ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች ጥቁር የታሪክ ጠባሳ ጥሏል''-የቢሮ ኃላፊዋ
ባህር ዳር ነሐሴ 20/2013 ( ኢዜአ) ''አሸባሪው ህወሃት ወሯቸው በነበሩ አካባቢዎች በህዝቡ ላይ ያደረሰው ሰብዓዊ፣ ሞራላዊና የንብረት ውድመት የቡድኑን የነቀዘ ሃሳብ በተጨባጭ ያሳየና ጥቁር የታሪክ ጠባሳ የጣለ ነው'' የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብዙአየሁ ቢያዝን አስታወቁ።
የቢሮ ኃላፊዋ ከባህር ዳር ከተማ አመራሮች ፣ ነጋዴዎች፣ ወጣቶችና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር በመሆን አሸባሪ ቡድኑ በደቡብ ጎንደር ዞን በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች የዕለት ምግብ ድጋፍ ለማድረግ ተንቀሳቅሰው ነበር።
አሸባሪው ቡድን በየደረሰበት ጥቃቅን ነገሮችን ሳይቀር ንብረት በመዝረፍ፣ የአርሶ አደሮችን መኖሪያ ቤት በከባድ መሳሪያ በማፍረስና ከብቶችን በጥይት ደብድቦ መግደሉን በወቅቱ መመልከታቸውንና መገንዘባቸውን ሀላፊዋ ተናግረዋል።
'የቡድኑ አባላት ህዝቡን በመግረፍ፤ በመዝረፍና ከብቱን አርዶ በመብላት ግፍ መፈጸማቸውን ከተጎጂ አርሶ አደሮች መረዳታቸውን ገልጸዋል።
የህዝብ መገልገያ የሆኑ ባንክ፣ የትምህርትና የጤና ተቋማትን ንብረት ከመዝረፍ ባ ለፈ አፈራርሶና አውድሞ መሄዱን እንደተመለከቱም ኃላፊዋ ተናግረዋል።
ሀላፊዋ አክለው ''አሸባሪ ቡድኑ በተለይ ህሙማን ያለአድልኦ የሚገለገሉበትን የጤና ተቋማት መርፌ ሳይቀር በመዝረፍ አውድሞ መሄዱ ሰብዓዊነት የሌለው ፍጡር መሆኑን አረጋግጧል'' ብለዋል።
የጥፋት ቡድኑ የአርሶ አደሩን ሃብት እስከ መኖሪያ ቤት በማውደም በሰብዕናውና በሞራሉ ላይ ጉዳት ማድረሱን ወይዘሮ ብዙአየሁ አስረድተዋል።
''አሸባሪ ቡድኑ በደረሰበት ሁሉ በህዝቡ ላይ ያደረሰው ሰብዓዊ፣ ሞራላዊና የንብረት ውድመት የቡድኑን የነቀዘ ሃሳብ በተጨባጭ ያሳየና ጥቁር የታሪክ ጠባሳ የጣለ'' ብለውታል።
''ጦርነቱ ሞራላዊና ኢሞራላዊ በሆኑ አካላት መካከል የሚካሄድ በመሆኑም ትልቅ ዋጋ እያስከፈለን ነው'' ሲሉም ኃላፊዋ ተናግረዋል።
"የብዙሀን መገናኛ ዘርፉ ወራሪው አሸባሪ ቡድን እየፈፀመ ያለውን ግፍ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተከታታይ ማሳወቅ ይገባዋል " ሲሉ አመልክተዋል።
የአማራም ሆነ መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቡድኑ የባሰና የከፋ ጥፋት እንዳያደርስ አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።
ሀላፊዋ በማያያዝ ቡድኑን ለመደምሰስ በግንባር ከሚያደርገው ፍልሚያ በተጨማሪ የውስጥ ባንዳዎችን አጋልጦ መስጠት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ሕዝቡ በግንባር ተሰልፎ ከጠላት ጋር እየተዋደቀ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ኃይሎችና ሚሊሺያዎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ሀላፊዋ ጥሪ አስተላልፈዋል።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአማራ ክልል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ማስከተሉ ይታወሳል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክተት ጥሪን ተከትሎ ሕዝቡ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ወራሪውንና ዘራፊውን ቡድን ክክልሉ ለማስወጣት እየታገለ ነው።