ቀጥታ፡

ለሃገሬ የነ የመንና ሶሪያን እጣ የተመኘላትን አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት መዝመት እሻለሁ

  ሀብታሙ ገዜ (ድሬዳዋ ኢዜአ)

አሸባሪው ህወሃት ሀገሬን እንደ ሶሪያና የመን ከሚያደርጋት ግንባር ዘምቼ ህይወቴን ለሀገሬ ታላቅነት ብሰጥ ይሻለኛል ትላለች ባለቤቷን ወደ ግንባር የሸኘች የሶስት ልጆች እናት።

ሀገር የሁሉንም ልጆቿን ትብብርና መደጋገፍን የምትሻበት ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡

መተባበር በጦር ግንባር ያሉትን ማገዝ ብቻ ሳይሆን ሰው በተሰማራበት መስክ ሁሉ ሀገርን እና ዜጎችን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ማድረግም ሌላው መንገድ ነው፡፡

በ1990 ዓ.ም. በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ሀገራቸውን አገልግለው በተለያዩ ምክንያቶች ከሠራዊቱ የተሰናበቱ ዛሬ ደግሞ እናት ኢትዮጵያን ከአሸባሪው ህወሓት ሊታደጉ በቅርቡ ወደ ግንባር ካቀኑት ጀግኖች መካከል የድሬዳዋ የቀድሞ ሠራዊቱ አባላት ይገኙበታል። 

ሁሉም ለእናት ሀገራቸው ማሸነፍና ሉአላዊነት መከበር ድምጻቸውን በህብረት ሲያሰሙ አንዳች ስሜት ውስጥ ይከታል።

በድሬዳዋ አስተዳደር ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ በሾፌርነት ሲያገለግል የቆየው ቴዎድሮስ ሰኢድ  ድንገት እናት ሀገርን የማዳን ጥሪ ሲሰማ ፍቃደኝነቱን ለማሳየት የቀድመው የለም። 
በ1990 ዓ.ም የባድሜ ጦርነት ወቅት ለእናት ሀገሩ በወታደርነት በማገልገል ለሀገር የሚሰጥን ክብርና ፍቅር በእሳት ውስጥ አሳይቷል፡፡

በወቅቱ በነበረው ጦርነት በመቁሰሉ ከሠራዊቱ በመሰናበት አዲስ ህይወት ጀምሯል፡፡በሾፌርነት ሙያ በመሰማራትም ትዳር መስርቶ የሦስት ልጆች አባት ሆኗል።

ቴዎድሮስ "የእናት ሀገሬን መደፈር ዜና ስሰማ አበገነኝ፤ ቆጨኝ፣ በባንዳ ሀገር ስትታመስ፣ ሰላሟ ሲናጋ እረፍት የሚሰማው ያለ አይመስለኝም " ብሎ ለውድ ሀገሩ ሊዋደቅላት ዳግም ቆርጦ ተነሳ።

ከሃዲው አሸባሪው ህወሃተ በሠራዊቱና በዜጎች ላይ በፈጸመው አሰቃቂ ግድያና ወንጀል በእጅጉ በማዘኑ ዛሬም ወደ ግንባር በመጓዝ የሀገሩን ሉአላዊነት ለማስከበር በወኔ መነሳቱን ይገልጻል።

በቅርቡ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ጥንት ጀግኖች አባቶች በወኔ በተሞሉና በእናት ሀገር መደፈር በበገኑ ቆራጥ ዘማቾች ደምቆ ነበር፤ ወደ ግንባር ሊሸኙ፤ ሁሉም ለእናት ሀገራቸው ማሸነፍና ሉአላዊነት መከበር ድምጻቸውን በህብረት ሲያሰሙ አንዳች ስሜት ውስጥ ይከታሉ።
ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ የትኛውንም መስዋዕትነት ከፍለው የሀገራቸውን አሸናፊነት ለማረጋገጥ ጉጉታቸው ይደንቃል፤ያኮራል፤ ከፍ ሲልም የየትኛውንም ሰብአዊ ፍጡር እንባ ይጎተጉታል፤ ይበልጡኑ በ"እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም" ዜማ ታጅበው በህብረት ለሀገር የሚሰጥን ፍቅር ለዜጎች ነጻነት የሚከፈልን መስዋዕትነት ሲያስተጋቡ ደጋግሞ ልብን ያሞቃል። 

ኢትዮጵያ እንዲህ ለህልውናዋ ህይወታቸውን የሚሰጡ፤ ክፉ አሳቢዎቿን የሚያንቆራጥጡ ጀግኖች እያሏት በምንም ሁኔታ አትፈርስም ከዛሬ ሃያላን ቀድማ ሃገር ነበረች ወደ ፊትም ትኖራለች። 

ሾፌሩ ቴዎድሮስ ወደዚህ የሽኝት ቦታ የመጣው በሶስቱ ልጆቹ ፣ በባለቤቱና በአባቱ ታጅቦ ነበር። እነሱም ጀግናን ወደ ስራው የመሸኘት ክብርን ተላብሰው ቁጭታቸውን እንዲመልስ ጠላታቸውን እንዲደመስስ በድል ርሃብ ተመስጠው ነበር የሸኙት። ሃገር ከሌለ ቤተሰብ፣ ሃገር ከሌለ ልጅ ማሳደግ፣ ሰርቶ በክብርና በሰላም መኖር እንደሌለ ከአባታቸው የቀደመ ታሪክ የተረዱት ልጆችም እንደ ልጅ ካሁኑ ቢናፍቁትም የትና ለምን እንደሚሔድ ተረድተዋል።

እሱም ይሄንኑ ነበር ያላቸው "ሀገር ከሌለ ምንም የለም፤ ሀገር በእኛ መስዋዕትነት ፀንታ ትቆማለች፤ ሀገሬን ለማዳን ቤተሰቤን ተሰናብቼ መሄዴ ነው" 

" በአጭር ጊዜ የሀገራችንን ሉአላዊነትና ሰላም አስከብረን በእርግጠኝነት እንመለሳለን” ሲል ፍጹም እርግጠኛ ሆኖ ነው “እናቴ” የሚላት ባለቤቱም “ትክክል ነው” ዓይነት እይታዋን ከገጽታዋ የሚነበበው ቆራጥነት ያስታውቃል፤ ባለቤቷ ወደ ግንባር መጓዙ አስደስቷታል፡፡ 
ወይዘሮ ዘዴ ታምሩ ትባላለች፤ የአቶ ቴዎድሮስ ባለቤት፤ የጦርነት አስከፊነትን ታውቀዋለች ፤ ለሥራ ወደ ሶሪያና የመን በተጓዘችበት ወቅት በደንብ አስተውላለች፡፡ 

“ሰው ሰላሙ ካልተረጋገጠ መኖር ይከብደዋል፤ አሸባሪው ህወሃት ደግሞ ሀገር ሰላም እንዲሆን አልፈለጉም፤ ያለን አማራጭ ሰላምን በራሳችን ማስከበር ነው " ትላለች ወይዘሮ ዘዴ፡፡
ባሏ ወደ ግንባር እንዲጓዝ የፈለገችው በምንም መንገድ የሶሪያና የየመን እጣ ፋንታ ለሀገራችን እንዳይሆን በማሰብ ነው፤ በዚህ አታበቃም ወይዘሮ ዘዴ፤ ለሀገር ሉአላዊነት መከበርና ለሰላም መረጋገጥ የምትሰጠው ዋጋ በተለየ መንገድ ከፍ ይላል ነው ያለችው። 

"የደረሰ ልጅ ቢኖረኝ ወደ ግንባር እልከው ነበር አለች የአስር ዓመት እድሜ ያለውን ልጇን እየተመለከተች፤ ከባለቤቴ ጋር ለመዝመትም ፈልጌ ነበር” ያለችው ዘዴ ለጊዜው ለሕጻናት ልጆቿ ትንሽ አጠገባቸው ለመቆየት ማሰቧን በመግለጽ " አሸባሪዎቹ ህወሃቶች ሀገሬን እንደ ሶሪያና የመን ከሚያደርጓት አሁንም ቢሆን ግንባር ዘምቼ ህይወቴን ለሀገሬ ታላቅነት ብሰጥ ይሻለኛል፤ ለሃገሬ የነ የመንና ሶሪያን እጣ የተመኘላን አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት መዝመት እሻለሁ ብላለች።

የዚህ ቤተሰብ የሀገር ፍቅር የኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያት ሁሉ ማሳያ ነው፡፡
ታዳጊው ሮቤል ቴዎድሮስ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆነ "አባቴ ሀገሬን እንዲያድን ፈቅጄለታለሁ፤ እኔ መማር የምችለው ሰላም ሲኖር ነው ፤ ውሃ መጠጣት የምችለው ሰላም ሲኖር ነው፤ ሰላም እንዲኖር ደግሞ አባቴ መሄድ አለበት" በማለት ነው የአባቱን መዝመት ትክክለኛነት የሚናገረው ።
የ80 ዓመት እድሜ ያላቸው  የቴዎድሮስን አባት  አቶ ሰኢድ በሽርም ወደ ግንባር ለመዝመት ዳግም በተሰበሰቡ የሠራዊት አባላት መካከል ተገኝተዋል፡፡

"ልጄን በባድሜ ጦርነት ጊዜ እዚሁ አዳራሽ ውስጥ ነው የሸኘሁት ፤ ዛሬም የናት ጡት ነካሽ የሆኑ ሀገር አጥፊዎችን እንዲያጠፋ ልጄን ዳግም ለመሸኘት ነው የተገኘሁት " ብለዋል።


ገጽታቸው ላይ የሚነበበው ስሜታቸው፣ ንቃታቸው፣ እልሃቸውና ቁጭታቸውን ከመግለጽ ይልቅ ለእናት ሀገር ያላቸውን ጥልቅ ፍቅርና ክብር ከፍ አድርጎ ያሳያል።


የባሰ ከመጣ ሁላችንም እንዘምታለን፤ ለውጭና ለባንዳ ጠላቶቻችን ሀገራችን እንድትበተን አንፈቅድም " ነው ያሉት አቶ ሰኢድ፡፡

ሽኝቴ ልጄን ብቻ አይደለም ወንድሞቹን ጭምር ነው፤ ፈጣሪ በድል እንዲመልሳችው ዘወትር እፀልያለሁ ብለዋል፡፡

ይህ ክስተት የቴዎድሮስ ብቻ ሳይሆን የተቀሩትም ዘማቾች የህይወት ታሪክ ተመሳሳይ መንፈስ እንዳለው የኢዜአ ሪፖርተር ባደረገው ቃል መጠየቅ አስተውሏል፡፡

እነዚህ ዳግም እናት ሀገራቸው እንድታሸንፍ ተከብራና ታፍራ ወደ ጀመረችው የብልጽግና ጎዳና እንድትራመድ መስዋዕት ለመሆን ዝግጁ ከሆኑ ወንድሞች ሌሎቻችን ምን እንማር ማለትና መጠየቅ አሁናዊና ወቅታዊ ጉዳይ ነው ፡፡

ትልቁና መሰረታዊ ሀገራዊው አጀንዳችንም መሆን ያለበት ቤተሰቡ ለሀገር ህልውና ህይወቱን ለመክፈል በተግባር ያሳየበት ውሳኔ የሰመረ የሚሆነው ቢያንስ አንድም የሠራዊቱንና የዘማቾችን ቤተሰቦችና ልጆች በመንከባከብና በማገዝ ነው፡፡

አንድም ደግሞ ሀገርና ህዝብ የጣሉብንን ኃላፊነት በቅንነትና በታማኝነት ያለመታከት ስንወጣ ይሆናል፡፡

ይህ ሲሆን በተባበረ አንድነት ሀገርን ማሻገር ይቻለናል፤ ይህ ሲሆን ኢትዮጵያም እናቴ ታሸንፋለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም