አሸባሪው ህወሃት ከሰው ልጅ አልፎ በእንስሳት ላይ ሳይቀር ያሳየው ጭካኔ ታሪክ አይረሳውም - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃት ከሰው ልጅ አልፎ በእንስሳት ላይ ሳይቀር ያሳየው ጭካኔ ታሪክ አይረሳውም
እንጅባራ ነሐሴ 20/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ በህይወትና ንብረት ላይ ያደረሰው ጥፋት ሳይበቃው በእንስሳት ላይ ያሳየው ጭካኔ በታሪክ የማይረሳ መሆኑን የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ ገለጹ።
የቢሮ ሃላፊው ዛሬ በተከናወነው በክልሉ ፖሊስ ኮሌጅ የ8ኛ ዙር ልዩ ኃይል ምልምል ፖሊስ ሠልጣኞች ምረቃ ላይ እንደተናገሩት ሃገርን ከብተና ለመታደግ ከአሸባሪው ቡድን ጋር የሚደረገው ትንቅንቅ ወሳኝ ታሪክ የሚመዘገብበት ነው።
ዜጎችን ሀገር አልባ ለማድረግ የተነሳውን እብሪተኛ መመከትና ልኩን ማሳየት ወቅቱ የሚጠይቀው ሀላፊነት መሆኑንም ተናግረዋል።
ጁንታው በአማራ ህዝብ ላይ ያልጠነሰሰው ሴራ ያላሳየው የግድያና የዘረፋ አይነት የለም ያሉት ኃላፊው በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ የፈጸመው የጭካኔ ድርጊት የታክ ጠባሳ ሆኖ ሲታወስ እንደሚኖር አስረድተዋል።
ፖሊስ ኮሌጁም በተለያየ ጊዜ ማህበረሰቡን በየትኛውም መንገድ ሳያለያዩ በእኩልነት እያገለገሉ ያሉ ፖሊሶችን እያፈራ ያለ መሆኑን ገልጸው የዛሬ ተመራቂዎችም ወቅታዊ ችግሩን ለመፍትት ከፍትኛ ሃላፊነት እንደተጣለባቸው ገልጸዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌውም በበኩላቸው አሸባሪው ህወኃት በለውጥ ሂደቱ በፖለቲካ መድረክ ተሸንፎ ከወጣ በኋላ ሽንፈቱን በኃይል ለማስመለስ በአማራና አፋር ህዝቦች ላይ ችግር እያደረሰ ይገኛል።
ከታሪክ ባለመማር የኢትዮጵያን ለውጥና ዕድገት ከማይፈልጉት ጋር ተሰልፎ የሀገር ክህደት ጥጉን እያሳየ ያለ ባንዳ የደቀነውን የጥፋት ተልዕኮ መላው ኢትዮጵያዊ እንዲመክጥም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ደግሞ ኃይልን ማጠናከር ለጸረ-ህዝብ የትህነግ ቡድን ወቅታዊ ምላሽ ነው” ብለዋል።
“ህዝባችን ለሠላም ከፍተኛ ዋጋና ትኩረት በመስጠት ለአገራችን ዘላቂ ልማት ቢመኝም በተቃራኒው በቆሙት እየተረበሸ ይገኛል” ብለዋል።
ከአባቶቻችን በወረስነው ጀግንነት አሸባሪውን በመከላከልም ሆነ መልሶ በማጥቃት በማንኛውም ቦታና ጊዜ ዜጎች ያለምንም የጸጥታ ስጋት በሠላም ወጥተው እንዲገቡ የማድረግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የክልሉ ልዩ ሃይል ፖሊሶች ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የሚወስዷቸው የህግ ማስከበር እርምጃዎች የሚፈልገውን ድል ለማምጣት ድርሻቸው የጎላ እንደሚሆንም አስረድተዋል።
አሸባሪውን ቡድን ቀድሞ ከመከላከል ባለፈ ህግ ፊት አቅርቦ እንዲዳኝ እንዲሁም የክልላችንንና የሀገራችንን ክብር የሚያስጠብቅ ወዳጅና ጠላት ለይቶ በሀገሩ ላይ የማይደራደር ልዩ ሀይል ፖሊስ ማጠናከርን ክልላችን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው።