ቀጥታ፡

ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ያዘጋጃቸው ችግኞች ለጎረቤት ሀገራት በመላክ ትስስር ለመፍጠር እየሰራ ነው

ጂንካ ፤ ነሐሴ 20/2013 (ኢዜአ) ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ያዘጋጃቸው 30 ሺህ የሚጠጉ ሀገር በቀል ችግኞችን ለኬንያ እና ደቡብ ሱዳን በመላክ ከአገራቱ ጋር የጠበቀ ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በሚገኝበት ደቡብ ኦሞ ዞን በአረንጓዴ አሻራ መረሃ-ግብር የዛፍና ፍራፍሬን ጨምሮ ከተተከሉ 66 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ 85 በመቶው ማጽደቅ ተችሏል፡፡

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በዞኑ በተካሄዱ የችግኝ ተከላ ሥራዎች እየተሳተፉ ሲሆን ፤ ዛፎችን መትከል ፋይዳው ዘርፈ ብዙ  ነው።

"የአካባቢ አየርን ለሰው ልጆች ምቹና ተስማሚ ከማድረግ ባለፈ የተፈጥሮ  ሚዛንን  በመጠበቅ በኩል የጎላ ጠቀሜታ አለው" ነው ያሉት።

የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለው አስተዋጾም እንዲሁ።

እንደ ዶክተር ኩሴ ገለጻ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የችግኝ ጣቢያ  የተለያዩ ችግኞችን  በማፍላት ለዞኑ እያቀረበ ይገኛል።

በተጨማሪም 30 ሺህ የሚጠጉ ሀገር በቀል ችግኞችን በማዘጋጀት ለኬንያ  እና ደቡብ  ሱዳን በመላክ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጠበቀ ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ደቡብ ኦሞ ዞን የአካባቢ ጥበቃ፣ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ጽህፈት ቤት የደን ባለሙያ አቶ መላኩ በበኩላቸው፤  በዞኑ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም ከ66 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በግለሰቦች፣ በተቋማትና በወል መሬቶች ላይ መተከላቸውን  አስረድተዋል፡፡

ከተተከሉ ችግኞች መካከል ኮሶ፣ ዝግባና ዋንዛ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ  ሥራዎች  የሚያገለግሉ ሲሆን፤ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ብርቱካን፣ አቮካዶና መሰል የፍራፍሬ ችግኞችም ይገኙበታል።

የተተከሉ ችግኞችን ከ400 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የዞኑ ነዋሪዎች በባለቤትነት ተረክበው እንዲንከባከቡ በመደረጉ በአሁኑ ወቅት 85 በመቶው ማጽደቅ መቻሉን ነው ባለሙያው ያስታወቁት።

የጂንካ ከተማ ነዋሪ ወጣት ዮሴፍ ፀደቀ በሰጠው አሰተያየት፤  በችግኝ ተከላ ከመሳተፍ ባለፈ የተተከሉትን በመንከባከብ ሃላፊነቱን   እየተወጣ መሆኑን ተናግሯል።

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለተተከሉ ችግኞች በወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በኩል ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን እየተንከባከበ እንደሚገኝ ን ነው ያስረዳው።  

በዘመቻ ከሚተከለው ችግኝ በተጓዳኝ በመኖሪያ ግቢው የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን ማልማቱን የገለጸው ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ማሙሽ ተዘራ ነው።

ለችግኞች ተገቢ እንክብካቤ በማድረገም ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ሥራ እያከናወነ ነው።

"የተከልኳቸው ችግኞች ጸድቀው በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛ፤ በመጪው ዓመት የምስራች ምርት ይሰጣሉ  ብዬ እጠብቃለሁ" ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም