በአሸባሪው ሸኔ የሚፈጸም የፀጥታ ችግር ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው- አስተዳደሩ - ኢዜአ አማርኛ
በአሸባሪው ሸኔ የሚፈጸም የፀጥታ ችግር ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው- አስተዳደሩ
ፍቼ ነሐሴ 20/2ዐ13 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአሸባሪው ሸኔ የሚፈጸም የፀጥታና የዘረፋ ችግር ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አጥናፉ በቀለ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ ወረ ጃርሶ፣ ኩዩና ደገም ወረዳዎች የአሸባሪው ሸኔ አባላት የሚፈጥሩትን የፀጥታ ችግር ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአካባቢ ሚኒሻ፣ በፖሊስና በህብረተሰቡ ትብብር እየተሰራ ነው፡፡
በተለይም አልፎ አልፎ ከኢዲስ አበባ፣ ጐጃም የሚወስደው አውራ ጐዳናን ተከትሎ የትራፊክ ፍሰቱን ለማስተጓጐልና ለማስቆም የሚጥሩ አካላትን ሴራ ለማክሸፍ መረጃ በመለዋወጥና በግንባር በመፋለም ህገ-ወጥ ድርጊቱን ለማስቆም እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በአንዳንድ የገጠር ቀበሌዎችና ከተሞች እንዲሁም አውራ ጐዳናው ላይ አሸባሪው ሸኔ የሰው ህይወት ያጠፋበት፣ የጭነትና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን ያቃጠለበትና ዘረፋ የፈፀመበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል።
"ቡድኑ አሁን ላይ "ለኦሮሞ ሕዝብ ነው የምታገለው" የሚለውን ጊዜው ያለፈበት የኢትዮጵያ ጠላቶች አፍራሽ አጀንዳ በማንገብ ልዩ ልዩ የጦር መሣሪያ በመያዝ ጫካ በመግባት የሽብር ስራውን የቀጠለ መሆኑን አቶ አጥናፉ ገልፀዋል፡፡
"በአሁኑ ጊዜ የአካባቢው አርሶ አደር የእርሻ ተግባሩን በሚፈፅምበት ወቅት የሰላምና የፀጥታ ችግር ለመፍጠር የሚጣጣረው ሸኔ የላኪውን የአሸባሪውን ሕወሃት ተልዕኮ ለመፈፀም እንጂ የኦሮሞን ጥያቄ ያነገበ አለመሆኑ ግልጽ ነው" ብለዋል፡፡
በህብረተሰቡና በፀጥታ ሃይሉ የተቀናጀ ስራ በመሰራቱ በአሸባሪው ቡድን ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ያስከተለ እርምጃ በቅርቡ መወሰዱን አመልክተዋል፡፡
የሀገሪቱን ህልውና እየተፈታተነ ያለው የትህነግ ተላላኪ ሸኔ የሽብር ተልዕኮውን የሚፈፅመው በሰላማዊ ዜጐች ላይ በመሆኑ የዞኑ ማህበረሰብ በመደራጀት አካባቢውን እንዲጠብቅ የማደራጀት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
አሸባሪው ህወሃትም ሆነ ሸኔ ሰላምን ማደፍረስና ፀጥታን ማወክ መገለጫ ባህሪያቸው በመሆኑ ሕዝቡ አንድነቱን በማጠናከርና ከመንግስት ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ እንደሚገባ ያሳሰበው ደግሞ የዞኑ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ሸመልስ ጣፋ ነው፡፡
ወጣቶች የሚቀርብላቸውን ሀገራዊ ጥሪ ተቀብለው ሕዝባቸውን ለማገልገል እንዲዘጋጁ በማህበሩ በኩል የማንቃትና የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የዞኑ ሀገር ሽማግሌ አቶ ማሞ በላቸው በበኩላቸው መንግስት የሸኔ አካላትን ሲገስጽና ሲመክር መቆየቱን ጠቁመው መንግስት ያሳየውን ትእግስት ከፍርሃትና ከአቅም ማነስ መቁጠር ኢትዮጵያዊ ባህል እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡
“አክራሪነትና ፅንፈኝነት ለማንም አይበጅም” ያሉት አቶ ማሞ ሸኔ በየአካባቢው ከሚፈፅመው አፍራሽ ድርጊት እንዲቆም ቡድኑን በተደራጀ አግባብ በሕዝብ ክንድ መደምሰስ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ህዝቡ በአካባቢው የሚከሰት የፀጥታ ችግር ለመግታት በመንግስት በኩል ብቻ የሚቀርብለትን ትክክለኛ መረጃ መቀበል እንዳለበት መክረዋል፡፡