ቀጥታ፡

አንዳንድ የትግራይ ዳያስፖራ አባላት የትግራይ ሕዝብ ስቃይ እንዲቀጥል ከአሻባሪው ሕወሓት ጋር መተባበራቸው የሚያሳዝን ነው

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 20 ቀን 2013 (ኢዜአ) አንዳንድ የትግራይ ዲያስፖራ አባላት "ራሳቸው የተደላዳለ ሕይወት እየኖሩ የትግራይ ሕዝብ ከስቃይና መከራ እንዳይወጣ ሲሰሩ ማየት ያሳዝናል" ሲሉ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ እስፈጻሚ ተናገሩ። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ውሰጥ ያለውን እውነታ በአግባቡ ሊረዳ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ የትግራይ ሕዝብ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክተው ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ዶክተር አብርሃም አሸባሪው ሕወሓት ላለፉት 50 ዓመታት ስሙን ከትግራይ ሕዝብ ጋር አቆራኝቶ ቢጠቀምም "አንድም ቀን አጀንዳውን የትግራይ ህዝብ አድርጎት አያውቅም" ይላሉ።

የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ የአሻባሪው ሕወሓት ሴራና ክፋት ሰለባ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።

ሕዝቡ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን በተለየ መልኩ ምንም ጥቅም አለማግኝቱ እየታወቀ "በትግራይ ዲያስፖራ በኩል እየተሰራ ያለው ስራ እጅግ ያሳዝናል" ብለዋል ዶክተር አብርሃም።

አንዳንዱ ዲያስፖራ በተሻለ አገር የተደላዳለ ኑሮ እየመራ የትግራይ ሕዝብ ስቃይ ማብቂያ እንዳይኖረው የሽብር ቡድኑን እያገዘ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።

"ሕዝብ በየደቂቃው እየታረደ፣ ሕጻናት እየረገፉ ምንም የማይመስላቸው የትግራይ ተወላጆች እጅግ የሚያሳዝን ተግባር እየፈጸሙ ነው" ብለዋል።

ይህም ውክል ናቸው ለትግራይ ሕዝብ ሳይሆን ለአሸባሪው ሕወሓት መሆኑን በግልጽ እንደሚያሳይ ነው የገለጹት።

አሸባሪው ሕወሓት "በሴራና በአፈና" ሕዝቡን ሲያስተዳድር መቆየቱን ያስታውሱት ዶክተር አብረሃም፤ አሁንም የትግራይ ሕዝብ ምንም ዓይነት አማራጭ መረጃ እንዳያገኝ መደረጉን ገልጸዋል።

በቅድሚያ የትግራይ ሕዝብ ስለ አሸባሪው ሕወሓት የተንኮል ገመና በግልፅ እንዲረዳ ተባብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጠውታል።

ይህ ከሆነ የትግራይ ሕዝብ አሸባሪውን ከራሱ ላይ ነቅሎ ለመጣል ወደ ኋላ የማይል ሕዝብ እንደሆነ በተግባር የተረጋገጠ ነው በማለት ያስረዳሉ ዶክተር አብረሃም።

የኢትዮጵያ ሕዝብም ቢሆን "የትግራይን ሕዝብ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር አያይዞ ሊመለከተው አይገባም" ይላሉ ዋና ስራ አስፈጻሚው።

የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገሩ የሚኮራ፣ በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና የተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል።

ምንም እንኳን አሸባሪው ሕዝቡን መከታ ለማድረግ ቢንቀሳቀስም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አጥፊዎችን ከሰላማዊ ዜጎች መለየት መቻል እንዳለበትም ተናግረዋል።

''በተለያየ መልኩ በሽብር ቡድኑ ኔት ወርክ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ካሉ እነሱን ማጋለጥ ያስፈልጋል፤ ከሃዲ የትም ሊገኝ ስለሚችል'' ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ ይህ አስቸጋሪ ጊዜ የሚያልፍ በመሆኑ ሕዝብን እንደ ጥፋተኛ መቁጠር ሳይሆን ቀርቦ ማገዝ ላይ ማተኮር አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዶክተር አብረሃም አክለውም የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም ቢሆን "መሬት ላይ ያለውን እውነታ ከመቀበል ይልቅ ድብቅ ፍላጎቱን ለማሟላት እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ የፌዴራል መንግስት ጊዜያዊ አስተዳደር አቋቁሞ የትግራይን ሕዝብ ከችግር ለመታደግ ሲሰራ ምስጋና ማቅረብ አለማቻሉን እንደማሳያ ጠቅሰዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እርዳታ በስፋት እንዲዳረስ ከማድረግ ጀምሮ ተቋርጠው የነበሩ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ጭምር መልሶ አስጀምሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

"ይህ ሁሉ ሆኖ አለም አቀፉ ማሕበረሰብ ነቀፌታን ነበር የመረጠው፤ ዛሬ ግን የትግራይ ሕዝብ የከፋ ስቃይ ውስጥ ሆኖ ምንም አይመስላቸውም'' ሲሉ በቁጭት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም