ቀጥታ፡

ሀገር ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ መጠቀሚያ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን አልታገስም- አስተዳደሩ

ዲላ ነሀሴ 20/2013 (ኢዜአ) ሀገር ያለችበትን ሁኔታ መጠቀሚያ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን አልታገስም ሲል የጌዴኦ ዞን አስተዳደር አሳሰበ።

በዞኑ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር የንግዱ ማህበረሰብ አካላትን ያሳተፈ የውይይት መድረክ በዞኑ ወናጎ ከተማ ተካሄዷል።
የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ለምለም ከበደ በወቅቱ እንዳሉት በዞኑ ከምርት ከአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ባለፈ ህገወጥ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችና ደላሎች መበራከት የዋጋ ንረቱን አባብሶታል።
መምሪያው ባደረገው ክትትል በከተሞች በተለይም በዲላና ይርጋጨፌ በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ነዳጅ ማገኝቱን ጠቅሰዋል።
ሀገር ያለችበትን ሁኔታ መጠቀሚያ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ጠንካራ ክትትል በማድረግ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ ሀላፊዋ አሳስበዋል።
በተለይ በጦርነት ምክንያት መንገድ ተዘግቷል በሚል የሀሰት መረጃ ምርት በማከማቸት ህገወጥ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ከንግድ ህጉ ባለፈ ከአሸባሪው ጋር በማበር ወንጀል በሽብር ህጉ የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑን አመልክተዋል።
ሀገር በህልውና ትግል ውስጥ እያለች ዋጋ በማናር የግል ሀብትን ከማካበት ባለፈ ህዝብን ለማስነሳት የሚቀሳቀሱ ነጋዴዎች ከአሸባሪው ህወሀት ተለይተው እንደማይታዩ የተናገሩት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽፈራው ቦጋለ ናቸው።
በህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ የኢትዮጵያ አሸናፊነት እንደማይደናቀፍና የህወሀትና ሸኔ ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ እንደማይሳካ ገልጸዋል።
በህገወጥ ተግባር የተሳተፉ ነጋዴዎች እንዲሁም ተግባሩን አይተው በቸልተኝነት ያለፉ የመንግስት ተቋማት ከተጠያቂነት እንደማይድኑ አስታውቀዋል።
የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሳሙኤል በፍቃዱ በበኩላቸው በግንባር ለሚዋደቁት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ደጀን መሆን ሲገባ ዋጋ በማናር የግል ጥቅምን ማሳደድ ከወንጀል ባለፈ የስነ ምግባርና የሞራል ውድቀት መሆኑን ተናግረዋል።
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም የንግዱ ማህበረሰብ ህገ ወጥ ነጋዴዎችን በማጋለጥ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
በመድረኩ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ ባለሃብቶች፣ የዞን፣ የከተማና የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የጸጥታና ሌሎች ባለደርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም