የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች አሸባሪውን ህወሃት ለመደምሰስ በሚካሄደው ትግል ለመሳተፍ ተነሳስተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች አሸባሪውን ህወሃት ለመደምሰስ በሚካሄደው ትግል ለመሳተፍ ተነሳስተዋል
አሶሳ ፤ ነሐሴ 20 / 2013(ኢዜአ) /ኢዜአ/ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል እስከ ግንባር በመዝመት አሸባሪውን ህወሃት ለመደምሰስ በሚካሄደው ትግል ለመሳተፍ መነሳሳታቸውን የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች አስታወቁ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ዛሬ በጤና ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 96 ተማሪዎች አስመርቋል፡፡
ተማሪ ዮርዳኖስ ጀምበር በዩኒቨርሲቲው 3 ነጥብ 9 በማምጣት በማዕረግ የተመረቀችው ስትሆን አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራ እንደማይሳካ ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት በቁጭት ገልጻለች፡፡
ከምረቃ በኋላ ወደ ስራ የመግባት እቅድ የሚሳካው የሃገር ደህንነት ሲጠበቅ እንደሆነ ነው ዮርዳኖስ የተናገረችው፡፡
ሴትነት ምንም ከማድረግ አግዶኝ አያውቅም የምትለው ተመራቂዋ፤ አሸባሪውን ህወሀት በመደምሰስ ሃገር የሚስፈልጋት ሠላም ለመመለስ በግንባር ጭምር በትግሉ ለመሳተፍ ተነሳስታለች፡፡
ይህ ደግሞ የየትኛውም ሃገር ዜጋ የሃገሩን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያደርገው ነው ብላለች፡፡
በዩኒቨርሲቲው ከነርሲንግ ትምህርት ክፍል በ3 ነጥብ 71 በማምጣት ተመረቀችው ወጣት ኤደን አስራት ደግሞ በማዕረግ መመረቋ እንዳስደሰታት ገልጻለች፡፡
ደስታዬ የተሟላ እንዲሆን የኢትዮጵያ ሠላም ሊመለስ ይገባል ነው ያለችው፡፡
ከየትኛውም ሙያ በላቀ በአሁኑ ወቅት ሃገር ለጤና ባለሙያዎች ጥሪ እያቀረበች ነው የምትለው ኤደን፤ የጥፋት ቡድኑ ህወሃት ከኢትዮጵያ ምድር እስኪወገድ በግንባር ተገኝቼ የሃገር መከላከያ ሠራዊትን ከማከም ባለፈ እዘምታለሁ ብላለች፡፡
ሌላዋ ተመራቂ እመቤት ወርቁ በበኩሏ፤ የዘንድሮ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ሀገርን የማስቀደም አደራ ተጥሎብናል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ያሳለፍኩት አራት ዓመታት ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን እንዴት ማለፍ እንዳለብኝ አስተምሮኛል ነው ያለችው፡፡
ይህን ተሞክሮ አሸባሪውን ህወሀት በመደምሰስ ሃገርን ለማስቀጠል ኢትዮጵያውያን በሚያደርጉት የህልውና ትግል በመሳተፍ የድርሻዋን ለመወጣት መነሳሳቷን ነው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተናገረችው፡፡
በቤተሰቡ ከእርሱ በቀር አብዛኞቹ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እንዳልተከታተሉ የሚገልጸው ደግሞ ከደቡብ ሱዳን በስደተኛነት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የነጻ ትምህርት እድል ያገኘው ወጣት ማጆግ ደንግ ነው፡፡
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ከዛሬ ተመራቂዎች መካከል 3 ነጥብ 98 በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ ጭምር በመሆን ነው፡፡
ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የተፈጥሮ ሃብታቸውን ያለማንም ፈቃድ የመጠቀም መብት እንዳለቸው ወጣት ማጆግ ይናገራል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ እንደሃገር የገጠማት ችግር ዋነኛ ምክንያት የተፈጥሮ ሃብቷን ተጠቅማ ከድህነት መላቀቅ መጀመሯ ያልተመቻቸው አካላት ሴራ እንደሆነም ወጣቱ ለኢዜአ ገልጿል፡፡
ይሁንና ኢትዮጵያውያን ፈተናውን አለፈው በድጋሚ ለአፍሪካውያን አርአያ እንደሚሆኑ እምነት አለኝ የሚለው ወጣት ማጆክ ፤በተለይም ሃገር ተረካቢ ወጣቶች እና አመራሩ ለመፍትሔው በእጅጉ ተናብበው መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲል መክሯል፡፡
ኢትዮጵያን እንደሁለተኛ ሀገሩ የሚያየው ወጣቱ ለተደረገለት የትምህርት ድጋፍ ልባዊ ምስጋና አቅርቧል፡፡
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ረዳት ፕሮፌሰር አበራ ባይሳ፤ ዩኒቨርሲቲው ሃገራዊ ተልዕኮውን ለመወጣት የአስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቶ እየሠራ መሆኑን በምረቃው ስነ-ሰርዓት ላይ ገልጸዋል፡፡
ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ህብረተሰቡን በሃገራዊ ጉዳዮች እንዲወያይ በማድረግ የድርሻውን እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡
ዛሬ የተመረቁት 96 ተማሪዎች በነርስ፣ አዋላጅ ነርስ እና ጤና መኮንን ዘርፍ ትምህርታቸው የተከታተሉ መሆናቸውን የኢዜአ ሪፖርተር ከአሶሳ ዘግቧል፡፡