ቀጥታ፡

በግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተለያዩ አልሚ ባለሃብቶች እየገቡ ነው

ነሀሴ 20/2013 (ኢዜአ) በግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተለያዩ አልሚ ባለሃብቶች ወደ ስራ በመግባት ላይ መሆናቸው ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጋር በመተባበር በቅርቡ ወደ ስራ የገቡ የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማስተዋወቅ ያለመ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች ለማሳያ ከታቀዱት 4 የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል ከትግራይ ክልል በስተቀር ሶስቱ በቅርቡ መመረቃቸው ይታወሳል።

የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብሩ ወልዴ እንዳሉት በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ሼዶች የወሰዱና በራሳቸው ሼድ ለመገንባት መሬት የወሰዱ 21 ባለሃብቶች ይገኛሉ።

በፓርኩ ውስጥ የሚገኙትን 11 ሼዶች ባለሃብቶች ተረክበው ቡና፣ የአቮካዶ ዘይት፣ ማር፣ ወተትና ሌሎች ምርቶችን ለማቀነባበርና ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ የሚገኙ መኖራቸውን ገልጸዋል።

ሼድ ከተረከቡት ውስጥ 9 የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ናቸው።

የአቮካዶ ዘይት በማምረት ላይ የተሰማራው አንድ የውጭ ባለሃብት ምርቱን  ወደ ውጭ በመላክ ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ አስገኝቷል ብለዋል።

በቲማቲም፣ አቡካዶ ዘይት፣ በቡና ፣ ወተትና ሌሎች ማቀነባባሪያዎች ላይ ለመሰማራት 10 ባለሃብቶች ሼድ ለመገንባት መሬት መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮች ኮርፖሬሽን ቴክኒክ ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ኪዳኔ ምስክር በበኩላቸው በቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በርከታ ባለሃብቶች ለመግባተ ፍላጎት እያሳዩ ነው።

በፓርኩ የመጀመሪያው ምዕራፍ በለማው ቦታ 6 ባለሃብቶች ፕሮጀክት የገቡ  ሲሆን ሪች ላንድ የተሰኘ ካምፓኒ ከአኩሪ አተር ፓውደርን አቀነባብሮ ወደ ውጭ በመላክ ባለፈው ዓመት ከ12 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ አስገኝቷል ብለዋል።

በፓርኩ ገብተው ለመስራት በርካታ ባለሃብቶች ፍላጎት እያሳዩ ቢሆንም የሃይልና የግብአት አቅርቦት እጥረት እንዳለ አንስተዋል።

የኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አማካሪ አቶ መሃመድ ሃሰን በቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ 29 ባለሃብቶች ወደ ስራ ለመግባት መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ከተመዘገቡት መካከል ሁለቱ ስራ ለመጀመር ማሽን በመግዛት ላይ ሲሆኑ ሌሎችም በሂደት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ልማት ማስተባበሪያ ዳሬክተር አቶ አያልነህ አባዋ፤ በ3ቱ ፓርኮች ገብተው ለመስራት 111 የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃቶች በሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረው 23ቱ ሼድ እየገነቡ ይገኛሉ።

የባለሃብቶች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ማስተናገድ የሚያስችል የፍሳሽ ማስወገጃ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ቡልቡላ ግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል። 

የሃይል አቅርቦትን በተመለከተ እያንዳንዱ ፓርክ የሚፈልገውን 50 ሜጋ ዋት የሃይል መጠን ለማቅረብ ራሱን የቻለ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ በማስፈለጉ መንግስት ከሚመለከታቸው ጋር እየተሰራ መሆኑን ጨምረዋል።

የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሙሉነህ ወልደኪዳን ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅታቸው መደገፉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ለአራቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እስካሁን 25 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መንግስት ወጪ ያደረገ ሲሆን ከልማት አጋሮች ደግሞ 27 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ ተደርጎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም