ለኢኮኖሚ አሻጥር ምክንያት ሊሆኑ በሚችሉት ላይ መንግስት ክልከላ ማድረጉ ወቅታዊና ተገቢ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለኢኮኖሚ አሻጥር ምክንያት ሊሆኑ በሚችሉት ላይ መንግስት ክልከላ ማድረጉ ወቅታዊና ተገቢ ነው
አዲስ አበባ ነሀሴ 19/2013 (ኢዜአ) ለኢኮኖሚ አሻጥር ምክንያት ሊሆኑ በሚችሉት ላይ መንግስት ክልከላ ማድረጉ ወቅታዊና ተገቢ መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናገሩ።
መንግሥት በቅርቡ ለባንኮች ባወጣው መመሪያ መሰረት የቤት፣ መኪና፣ ሕንጻና የመሳሰሉትን እንደ መያዣ ተጠቅመው ከባንክ ብድር ለሚወስዱ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ብድር እንዳይሰጥ ክልከላ አድርጓል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አሻጥሮች እየተሰሩ መሆኑን ተከትሎ ወንጀሉን ለመከላከል ሲባል ባንኮች ብድር መስጠት እንዲያቆሙ መደረጉ ይታወቃል፡፡
መንግስት ክልከላ ያደረገው አንዳንዶች ቤታቸውን፣ መኪናቸውንና ሕንጻቸውን አስይዘው ከባንክ ብር በመውሰድ ዶላር እየገዙና የተለያዩ የወንጀል ተግባር አሻጥሮችን እየፈፀሙ መሆኑ ስለተደረሰበት ነው።
እየተፈፀመ ያለውን ወንጀል ለመከላከል ሲባል መንግስት የወሰዳቸውን የመፍትሄ ርምጃዎች በማስመልከት ኢዜአ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቸን አነጋግሯል።
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የልማት ኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ተስፋዬ ጮፈና፤ አገራት ለኢኮኖሚ አሻጥር ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ማናቸውንም ውሳኔዎችና ክልከላዎችን በማድረግ ኢኮኖሚውን የማረጋጋት ሥራ እንደሚተገብሩ ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ መንግሥት የኢኮኖሚ አሻጥሩን ለመከላከል ሲል በመሬት ሽያጭና በባንክ ብድር ላይ ያደረጋቸው ክልከላዎች ወቅቱን ያገናዘቡና ትክክለኛ ውሳኔዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።
ክልከላው ለአጭር ጊዜ ተግባራዊ ሆኖ በረጀም ጊዜ ሌሎች መፍትሄዎች በማምጣት መስራት ይገባል ብለዋል ዶክተር ተስፋዬ።
ሌላኛው የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ደረጄ ደጀኔ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ላለው የኢኮኖሚ አሻጥር ህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬ ዝውውር ዋነኛ ምክንያት ነው።
በመሆኑም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ውስጥ የሚልኩትን የውጭ ምንዛሬ (ሬሚታንስ) በባንኮች ብቻ በማድረግ ችግሩን ለመቀነስ ማገዝ አለባቸው ብለዋል።
ህገ ወጥ የዶላር ምንዛሬ በአገር ውስጥ የምርት እጥረት እና የዋጋ ንረት እንዲከሰት በማድረግ ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና የሚፈጥር መሆኑንም ያብራራሉ።
ግልጽ የሆነ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር፣ የዋጋ እና የምርት እጥረት እንዳያጋጥም፣ የጥቁር ገበያውን በመቆጣጠርና በማርገብ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።