ቀጥታ፡

“ጆሮ ዳባ ልበስ”-ለምን?

አሸባሪው ህወሓት በጥቅምት ወር በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘር የፈጸመው የሀገር ክህደት ተግባር ሉአላዊነትን የሚዳፈርና በየትኛውም ሀገር መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑ ምሁራን ይገልጻሉ።

ይህ ቡድን የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ ከበባ በማድረግ በሌሊት “እጃችሁን ስጡ ጠመንጃችሁን አስረክቡ፤ የእኛ መንግስት በህዝብ የተመረጠ የአዲስ አበባው መንግስት ግን በህዝብ የተመረጠ ስላልሆነ ፈርሷል" በሚል ነበር ጥቃቱን የጀመረው።

ይህ የሽብር ቡድን በማይካድራ ንጹሐን ዜጎችን ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ፈጽሟል።  በትግራይ ክልል የህዝብ መገልገያ የሆኑ የአክሱም ኤርፖርትን ጨምሮ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ እና ሌሎች የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል።

ከዚህ ባሻገር በክልሉ መረጋጋት እንዲመጣና ሕዝቡ ወደ መደበኛው ሕይወት እንዲመለስ ለማድረግ ሲሰሩ በነበሩ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲቪል አባላት ላይ እንዲሁም መንግስትን ደግፋችኋል ያላቸው በርካታ ንፁሓን ላይ በአደባባይ ግድያን ፈጽሟል። 

መንግስት የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ ያጣጣለው አሸባሪው ቡድን ሀገር ለማፈራረስ በነደፈው ሴራ በቅርቡ በአማራና አፋር ክልሎች ላይ በፈጸመው ትንኮሳ በርካታ ንፁሐን ዜጎች በጅምላ ተገድለዋል፣ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ ንብረት ወድሟል። በአማራ ክልል ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ሲፈናቀሉ በአፋር ደግሞ ከ70 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ሆነዋል።

ቡድኑ በራያ ቆቦ አጋምሳ የሚባለው መንደር በከባድ መሳሪያ በመደብደብ ሙሉ በሙሉ አውድሟል። ታጣቂዎቹ እሳት በእጃቸው ይዘው ቤት ለቤት በመዞር እያንዳንዱን ቤት በውስጥ ያለው የሰውና የእንሰሳት ህይወት ጭምር እንዲቃጠሉ አድርጓል።

በተመሳሳይ በአፋር ክልል በጋሊኮማ የሽብር ቡድኑ በከፈተው ጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች ተጠልለውበት በነበረው ትምህርት ቤት እና የጤና ተቋም ላይ በፈጸመው ጥቃት ከ100 በላይ ህጻናትን ጨምሮ ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

አሸባሪው ቡድን የፈጸማቸው ድርጊቶች በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት በወንጀል የሚያስጠይቅ ስለመሆኑ ብዙ የህግ አዋቂዎች ይስማሙበታል። ይሁን እንጂ አብዛኛዎቹ ምእራባውያን ሀገራት፣ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የሰብአዊ መብት ተቆርቃሪዎች እና የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ከእውነታው በተቃራኒ ቆመዋል።

እነዚህ አካላት አሸባሪው ህወሓት ሀገር ለማፍረስ አቅዶ እየሰራ መሆኑን በግልጽ እየተናገረና እየፈጸመ፤ አይተው እንዳላዩ ሆነዋል። ይልቁንም ከፌዴራል መንግስቱ ተቃራኒ በሆነ መንገድ በመቆም የተለያዩ ማእቀቦችን ከመጣላቸውም በላይ ኢትዮጵን ለመጉዳት ብዙ እርቀት ተጉዘዋል፡፡ በዚህ  አካሄዳቸው መላው ኢትዮጵያውያን ምእራባውያንን በጥርጣሬ እንዲያዩ አስገድዷቸዋል።

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶችም ይሁኑ አብዛኛዎቹ ለጋሾች በእርግጥ ለሰብአዊ መብት የሚገዳቸው ቢሆን አሸባሪው ቡድን የፈጸማቸው ወንጀሎች አንድ በአንድ ቆጥረው ተጠያቂ ማድረግ በቻሉ ነበር። ነገር ግን የወንጀል ድርጊቱን በመሸፈንና ሀገር የማፍረስ ዓላማውን በመደገፍ ተባባሪነታቸውን በማስመስከር ላይ ይገኛሉ።

እነዚህ ተቋማት በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር እርምጃ በተካሄደበት ወቅት በአሸባሪው ቡድን የተፈጸሙ ወንጀሎችን በግልጽ ሲያጋልጡ አልታዩም። ከዚህ በተቃራኒ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በመክፈት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተዛባ ምስል እንዲኖረው አበክረው ሰርተዋል። መንግስት እውነታውን ለማስገንዘብ በተደጋጋሚ የሰጣቸው መግለጫዎችም ይሁን ላከናወናቸው ተግባራት በሙሉ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋል።

ምእራባውያኑ መሬት ላይ ያለውን እውነታ መሠረት ከማድረግ ይልቅ በጦርነቱ ወቅት በንፁሐን ላይ ስለደረሰው ግድያ፣ ስለወደመው ንብረት፣ ስለተፈጸመው ዘር ተኮር ጥቃት፣ በሴቶች ላይ ስለደረሰው አስገድዶ መደፈር እና  የመሳሰሉት አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ ያደረጉት የኢትዮጵያን መንግስት ነው፡፡

ጉዳዩን ይበልጥ ለማወሳሰብ የኤርትራ ወታሮችንና የአማራ ሚሊሻዎችን ተጠያቂ አድርገዋል። እርዳታ እንዳይሰራጭ ክልከላ እንደተደረገ ዘመቻ ከፍተው አስተጋብተዋል። ጥፋት ፈፃሚው አሸባሪው ቡድን እንደ ተጎጂ በመቁጠር ተሟግተውለታል።

መገናኛ ብዙሃኑ የቡድኑን ጀግንነት በማጋነን ብዙ ቦታዎች እንደተቆጣጠረ ሲተርኩ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ደግሞ ለተጎጂዎች መድረስ የሚገባውን ድጋፍ ለአሸባሪው ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል።    

የኢፌዴሪ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ኤጀንሲ በነሐሴ ወር ሶስት የውጭ ድርጅቶች ከተቋቋሙለት አላማ ውጭ በመንቀሳቀሳቸው ከስራ ያገዳቸው መሆኑ ይታወሳል። እነዚህ ድርጅቶች MSF HOLLAND፣ NORWEGIAN REFUGEE COUNCIL እና AL MAKTOUME FOUNDETION ሲሆኑ ፍቃድ ሰጪው ተቋም ባደረገው ክትትል ከተቋቋሙለት አላማ ውጭ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማህበራዊ መገናኛ አውታር በማሰራጨት፣ ፈቃድ ያልተሰጣቸውን የውጭ ዜጎች ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት፣ ፈቃድ ሳይሰጣቸው የሳተላይትና የሬድዮ መገናኛ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት አፍራሽ ለሆኑ ዓላማ ሲሰሩ በመገኘታቸው ማገዱን አሳውቋል።  

በቅርቡ በአማራ ክልል ጋሳይ ግንባር ከተማረኩት መካከል የአሸባሪው ቡድን አባል ኮሎኔል ገብረህይወት ገብረአላፍ እጅ ሃይልና ሙቀት ሰጪ ምግቦች ተገኝተዋል። እነዚህ ሃይልና ሙቀት ሰጪ ምግቦች ዓለምአቀፍ የእርዳታ ደርጅቶች ለትግራይ ህዝብ ለማከፋፈል የወሰዷቸው ናቸው። መንግስት የትግራይ ክልልን ለቅቆ ከወጣ በኋላ እርዳታ በማሰራጨት ላይ የሚገኙት አምስት ድርጅቶች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአሸባሪው እጅ የተገኘው ሀይል ሰጪ ምግብ ድርጅቶቹ የሚሰጡት እርዳታ በትክክል ለተረጂዎች የማድረስ ግዴታቸውን ከመወጣት ይልቅ ለአሸባሪው በእጅ አዙር ድጋፍ መስጠታቸውን የሚያመለክት ተግባር ነው። እውነታው ይህ ቢሆንም ምእራባውያኑ አሁንም መንግስትን መውቀስ አላቆሙም።

ከሰሞኑ የአሜሪካ የዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት ዩ ኤስ ኤይድ ዋና ሀላፊ ሳማንታ ፖወር ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ ላይ በትግራይ ክልል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን በመጥቀስ እጥረቱ የተከሰተው “የኢትዮጵያ መንግሥት በማደናቀፉ ነው" በማለት ከሰዋል። ችግሩ የተፈጠረው አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል ላይ በፈጸመው ትንኮሳ ምክንያት መሆኑን መንግስት በተደጋጋሚ አሳውቋል። የዩኤስ ኤይድ ሀለፊ በዚህ መግለጫቸው ላይ አሸባሪው ህወሃት ስለፈጸማቸው ወንጀሎች ትንፍሽ አላሉም።

እዚህ ላይ መጠየቅ ያለበት ቁልፍ ጉዳይ ምእራባውያን በእርዳታ ሽፋን እንዴት አሸባሪዎችን የመቀለብ ያልተገባ ተግባር ውስጥ ሊገቡ ቻሉ? የሚለው ነው። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህን እውነታ አበክሮ ሊጠይቅ ይገባል።

የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ለመምከር እንደሚሰበሰብ ተሰምቷል። ስብሰባው እንዲካሄድ ጥሪ ያቀረቡት አየርላንድ፣ ኢስቶኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ኖርዌይ፣ ብሪታኒያ እና አሜሪካ መሆናቸውም ታውቋል። ምክር ቤቱ ከዚህ በፊት ባደረጋቸው ሰባት ስብሰባዎች የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑት እንደቻይና፣ ሩሲያ፣ ህንድ እና ኬንያ የመሳሰሉት እውነታውን በሚገባ አስገንዝበዋል። አሁንም እነዚህ ሀገራት ለእውነት እንደሚቆሙ ይታመናል።

የስብሰባው ውጤት ምን ይሆናል የሚለው ከወዲሁ መገመት ቢያዳግትም ጆሮ ዳባ ልበስ በሚል ያልተገባ አቅጣጫ እየተከተሉ ያሉት ምእራባውያንም የተሻለ አረዳድ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም