ፕሬዝዳንት ሙላቱ በኢትዮጵያ የሞዛምቢክ አምባሳደርን አሰናበቱ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ሙላቱ በኢትዮጵያ የሞዛምቢክ አምባሳደርን አሰናበቱ
አዲስ አበባ ግንቦት 8/2010 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በኢትዮጵያ የሞዛምቢክ አምባሳደር ማኑኤል ጆሴ ጎግላቭዝን አሰናበቱ። ፕሬዝዳንቱ ከአምባሳደሩ ጋር ሁለቱ አገራት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነታቸውን አጠናክረው መቀጠል በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል። በአምስት አመት የኢትዮጵያ ቆይታቸው የሁለቱን አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከማጠናከር ጀምሮ አገራቱ በኢኮኖሚ፣ በሰላምና መረጋጋት ላይ በጋራ እንዲሰሩ ማስቻላቸውን አምባሳደር ማኑኤል ጆሴ ጎግላቭዝን ገልፀዋል። በተጨማሪም በቆይታቸው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሞዛምቢክን እንዲጎበኙ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል። ሁለቱ አገራት የሰላምና መረጋጋት የጋራ ጥምር ኮሚቴ ማቋቋም፣ በባህልና ቱሪዝም፣ በተደራራቢ ቀረጥ ማስቀረት እንዲሁም በአየር ትራንስፖርት በጋራ መስራት የሚሉ ስምምነቶችን መፈራረም መቻላቸውንም አምባሳደሩ ገልፀዋል። ሞዛምቢክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በቀጣዩ ተተኪ አምሳደር አማካኝነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ያስታወቁት አምባሳደሩ፣ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል። በፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት የፕሮቶኮልና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት አገራቱ ያላቸውን ግንኙነት በላቀ ሁኔታ ለማጠናከር ስምምነት ላይ የደረሱባቸውን ጉዳዮች ወደተግባር መለወጥ እንደሚኖርባቸው ሁለቱም ወገኖች ሃሳብ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም በቀጣይ ከምስራቅ እስከ ደቡብ አፍሪካ ባለው ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሞዛምቢክ ዋነኛ መተላለፊያ በመሆኗ በጉዳዩ ላይ በጋራ ለመስራት ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ጥሪ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል። በሁለቱ አገራት መካከል ያሉ መልካም ተሞክሮዎች ልውውጥም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ነው ያሉት። ኢትዮጵያና ሞዛምቢክ ይፋዊ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት በ1977 ዓ.ም ነው።