ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሓት በግንባር ያጋጠመውን ሽንፈት በስነ ልቦና ጦርነት ለማካካስ እየሰራ ነው

ደብረ ማርቆስ (ኢዜአ) ነሀሴ 19/2013 አሸባሪው ህወሓት በግንባር ሽንፈት ሲገጥመው ሀሰተኛ መረጃዎችን በመልቀቅ በስነ ልቦና ጦርነት ለማካካስ እየሰራ ነው ሲሉ በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የምስራቅ ጎጃም ዞን ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ማናዬ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ አካሂዷል።

በደረሰባቸው አካባቢዎችም  ንጹሃንን በመግደል፣  ሃብትና ንብረት  በመዝረፍና  ህጻናትን ሳይቀር በመድፈር በክልሎቹ አሰቃቂ ወንጀሎችን እየፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።

የጥፋት ቡድኑ በግንባር ከመፋለም ይልቅ ከ30 ዓመታት በፊት በጫካ እያለ ይጠቀምበት የነበረውን ሃሰተኛ መረጃ በመልቀቅ አሁን ላይ እየደገመውና የስነልቦና ጦርነት እያካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል።

"ህወሓት በግንባር ባጋጣመው ሽንፈት ኮሎኔሎችና ሌሎች የጦር አዛዦቹን ጨምሮ በርካታ ታጣቂዎቹ ሙት፣ ቁስለኛና ምርኮኛ እየሆኑ ባለበት በአሁኑ ወቅት የፕሮፓጋንዳ ድል ማስተጋባቱ የትም አያደርሰውም" ብለዋል።

ህዝቡ ለአሸባሪው ህወሓት ፕሮፓጋንዳ ጆሮ ሳይሰጥ ወደ ግንባር በመዝመት፣ በአካባቢው ሰርጎ ገቦችን በመቆጣጠርና የደጀንነት ሚናውን በመወጣት አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንዳለበት አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።

"ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚለቀቁ ሃሰተኛ መረጃዎች ሳይደናገር ለህልውና ዘመቻው የሚጠበቅበትን ማበርከት አለበት" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ተወካይ አቶ ሰለሞን በጉልበት ናቸው።

የሚፈልገውን መረጃ ከመንግስትና ከህዝብ ብዙሀን መገናኛዎች ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመው፣ "ኢትዮጵያዊያን ትብብራቸውን ካጠናከሩ ባጭር ጊዜ ውስጥ የድሉ ተቋዳሽ መሆን ይቻላል" ብለዋል።

"አሸባሪው ቡድን ቦታዎችን እየለቀቀና እየሸሸ ባለበት በአሁኑ ወቅት ድል እንዳገኘ አድርጎ የፎቶ ግራፍ መረጃ መልቀቅ ያረጀና ያፈጀ ፕሮፓጋንዳ በመሆኑ መደናገር አያስፈልግም" ብለዋል።

የህውሓት ፕሮፓጋንዳ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር ተካፋዮች የተዘረጋ መረብ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባል አቶ ሞላ ተሾመ ናቸው።

አሁን ላይ ዜጎች በጋራ ህብረት ፈጥረው እያካሄዱት ባለው የግንባር ፍልሚያና በተገኘው ድል የህወሓት የሃሰት ፕሮፓጋንዳና የስነልቦና ጦርነት እየተናደ መምጣቱን ተናግረዋል።

የጥፋት ቡድኑ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ያካሄደውን ግድያ፣ ዝርፊያና ሌሎች ግፍና በደሎችን ለዓለም ህዝብ በማሳየት ዜጎች ሚናቸውን እንዲወጡ አመልክተዋል።

የህልውና ትግሉን በድል ለማጠናቀቅ በሚደረገው ርብርብ የፓርቲያቸው አባላትንና ደጋፊዎቻቸውን አስተባብረው በግንባር በመሰለፍ የደጀንነት ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም