የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ህልውና እንዲከበር አሸባሪው ህወሃት መጥፋት አለበት

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 19 ቀን 2013 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ህልውና እንዲከበር አሸባሪው ህወሃት መጥፋት አለበት" ሲሉ የአምባ ጊዮርጊስ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

አሸባሪው ህወሃት አገር የማፍረስ ሴራን ለመመከት መዘጋጀታቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የአምባ ጊዮርጊስ ከተማ ነዋሪዎች አሸባሪው ህወሃት አገር የማፍረስ ሴራ ለመመከት ወታደራዊ ሥልጠና በመከታተል ላይ መሆናቸውን ተመልክተናል።

በዚህ ወቅት ያነጋገርናቸው የአምባ ጊዮርጊስ ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ አይፈራም አየነው እንደተናገሩት፤ የከተማ ነዋሪዎች እንደ አገር የቀረበውን “ኢትዮጵያን ለማዳን የትም፣ መቼም በምንም እዘምታለሁ” ጥሪ ተቀብለው ሰራዊቱን እየተቀላቀሉ ነው።

የክልሉ መንግስት ያቀረበውን የክተት አዋጅ በመቀበል የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የታጠቁ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ወጣቶችና ጎልማሶች እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞች የጥፋት ቡድኑን ለመመከት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ግንባር የተላኩ የአካባቢው ሚሊሻዎች ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት ጠላትን ድል እያደረጉ እንደሚገኙም ገልፀዋል።

የከተማዋ ነዋሪ አቶ በላይ ዓለም እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ህወሃት አገር በሚያስተዳድርበት ወቅት ብዙ ግፍ እና በደል አድርሷል።

ቡድኑ ዳግም በኢትዮጵያ ምድር ላይ ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዳይፈፅም ለማጥፋት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

ወይዘሮ ሰናይት ጫኔ አቅም ያለው ሁሉ አሸባሪውን ቡድን ለማጥፋት መዝመት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።

አገር ለማፍረስ የመጣ ቡድንን ለመመከት "ግንባር ድረስ በመዝመት ሂሳባችንን እናወራርዳን" ሲሉ የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሀብቴ እዘዘው ተናግረዋል።

“የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ህልውና እንዲከበር አሸባሪው ህወሃት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መጥፋት አለበት”  ብለዋል።

ማንኛውም ወጣት አገር ያቀረበችለትን ጥሪ ተከትሎ "አገሩን ለማዳን መዝመት አለበት" ሲል ወጣት ተስፋሁን ጌትነት  ጥሪውን አቅርቧል።

አሸባሪው ህወሃት ግብዓተ መሬቱን ለመፈፀም ወታደራዊ ሥልጠና በመውሰድ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቁርጠኛ የህዝብ ልጆች አሸባሪው ህወሃት ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት ስልጠናውን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም