አሸባሪውን ሕወሃትን ለማጥፋት የተባበሩት ክንዶችና የኢትዮጵያ መጻዒ ዕድል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪውን ሕወሃትን ለማጥፋት የተባበሩት ክንዶችና የኢትዮጵያ መጻዒ ዕድል
ኢትዮጵያ እንደ አገር ከጸናች ጀምሮ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ያሉ ጠላቶች አገረ-መንግሥቱን ለማዳከም የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
አገሪቷ በህዝቦቿ የተባበረ ክንድ ለየትኛውም ኃይል ሳትንበረከክና ለማንም ሳትገዛ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በድል እየተወጣች ዛሬ ላይ መድረሷንም እንዲሁ።
''ኢትዮጵያዊነት አይበገሬነት'' መሆኑን ከኢትዮ-ጣልያን፣ ከኢትዮ-ሶማሊያና ከሌሎችም አገራት ጋር የተደረጉ ጦርነቶችን ማንሳት ብቻ በቂ ነው።
ወቅታዊ አገራዊ ጉዳይን አስመልክቶ ትናንት በብሔራዊ ቴአትር በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበት ጦርነት ለቀጣይ የአገረ - መንግሥት ግንባታ ይዞት የመጣው "ዕድል ወይስ ፈተና" የሚሉ ሐሳቦች የተነሱበት ነው።
የፍልስፍና መምህሩ ዶክተር ዳኛቸው ወርቁ እንደሚሉት፤ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተው ጦርነት በሁለት ገፊ ምክንያቶች የተጀመረ ነው።
አንዱና ዋነኛው ኢ-ፍትሃዊነትና ሌብነት ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ በህግና ሥርዓት አልገዛም ማለት ነው ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት እነዚህን ገፊ ምክንያቶች በተደጋጋሚ ሲፈጽም መቆየቱን አስታውሰው፤ በመላ አገሪቷ ያሉ ሃብቶችን በህገ ወጥ መንገድ ሲዘርፍና ለራሱ ጥቅም ብቻ ሲያውል እንደነበር አንስተዋል።
ጦርነት ለማንም የሚበጅ ባይሆንም በአገር ህልውና ላይ ሲመጣ ጦርነት ገጥሞ ህልውናን ማስጠበቅ ግድ መሆኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች ይገልጻሉ።
ጦርነት አውዳሚ በመሆኑ በብዙዎች ዘንድ ይወገዛል። ይሁንና ለጠንካራ አገረ-መንግሥት ግንባታና ለአንድ አገር ህልውና አዎንታዊ ሚና እንዳለው በአመክንዮ ይከራከራሉ።
የአንድ አገር ህዝብ አብሮነቱን የሚያሳየውና ወዳጅነቱን የሚያጠነክረው በጦርነት ጊዜ መሆኑን ገልጸው፤ "ከራስ ጥቅም በላይ አገር የሚቀድመውም በዚሁ ጊዜ ነው" ይላሉ።
ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አሁን የመጣው መከራ ለኢትዮጵያውያን የመርገም በረከት ያለው ነው ይላሉ።
ባለፉት ሦስት ዓመታትም ሆነ ቀደም ባሉት ጊዜያት ወጣቱ የአገር ፍቅር እንዲያድርበትና አንድነቱን እንዲያጠናክር የተሰሩ ሥራዎች ውጤት አለማምጣታቸውን ገልጸዋል።
ይሁንና ኢትዮጵያ በገጠማት የህልውና ፈተና ምክንያት በተጀመረው ጦርነት መልካም ዕድሎች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ በጦርነት ወቅት በእርዳታ ሰበብ የአገርን ሉዓላዊነት ለመድፈርና ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩ አገራት መኖራቸውን ያነሳሉ።
ይህን ፍላጎት ከአገር ህልውናና ጥቅም በላይ ማድረግ የከፋ ጉዳት እንደሚኖረው የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን፤ ኢትዮጵያ ለጥቅምና ለመደለያ ብላ ሉዓላዊነቷን አሳልፋ እንደማትሰጥ ይገልጻሉ።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የህግ ማስከበር የህልውና ዘመቻ መጀመሩ ይታወሳል።
ከዚህ ባለፈ አሸባሪ ቡድኑ ከትግራይ ክልል ውጭ በአማራና አፋር ክልሎች ትንኮሳ በመፈጸም በርካታ ንጹሃንን እየገደለና ንብረት እያወደመ ይገኛል።
ይህን ድርጊት ለማስቆምና የአሸባሪውን እኩይ ዓላማ ለማክሸፍ በመላው የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ዜጎች ''ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ! መቼም፣ የትም፣ በምንም!'' በሚል መርህ በጋራ ቆመዋል።