አሸባሪው ህወሓትን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመደምሰስ ፊታችንን ወደ ልማት እናዞራለን - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓትን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመደምሰስ ፊታችንን ወደ ልማት እናዞራለን
ነሃሴ 19-2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓትን "በአጭር ጊዜ ውስጥ በመደምሰስ ፊታችንን ወደ ልማት እናዞራለን" ሲል የኢፌዴሪ አየር ሃይል ገለጸ።
የኢፌዴሪ አየር ሃይል ኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክተር ኮሎኔል ተሾመ በዳዳ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት፤ አሸባሪው ህወሓት በስልጣን በቆየበት ወቅት አየር ሀይልን በትኖ እና ዘርፎ ወደ መቀሌ መሸሹን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ከለውጡ በኋላ በተቋሙ በተሰራው የሪፎርም ስራ አየር ሀይሉ በሙሉ ቁመናና ዝግጁነት ላይ ሆኖ እንዲደራጅ መደረጉን ነው ያብራሩት።
በዚህ ምክንያትም አሸባሪው ህወሓት አየር ሀይልን በትኖ እና ዘርፎ መሄዱን አስታውሰው፤ አየር ሃይሉ እርሱ ባስቀመጠበት ቦታ ያለ መስሎት በመጀመሪያው የህልውና ዘመቻ ወቅት ጦርነት መክፈቱን ነው የተናገሩት።
መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በማድረግ ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ አሸባሪው ቡድን በአጎራባች የሚገኙ የአማራና አፋር ክልሎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ነው የተናገሩት።
ይህ አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ ሃይሎች ጋር በመሰለፍ የተለያዩ የጥፋት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ነው ያነሱት።
ይሁን እንጂ የዚህ የሽብር ቡድኑ ዓላማ በጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊትና አገር ወዳድ ዜጎች የጋራ ትብብር እየከሸፈ መሆኑን ተናግረዋል።
ደጀን ህዝባችንን ይዘን በአጭር ጊዜ ውስጥ ጦርነቱን በመቋጨት "አሸባሪውን ህወሓት በመደምሰስ ፊታችንን ወደ ልማቱ እናዞራለን" ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በየትኛውም የጥፋት ሃይል የማትፈርስ ታላቅ አገር መሆኗን የተናገሩት የአየር ሃይል ኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክተር ኮሎኔል ተሾመ በዳዳ በቡድኑ ላይ በጋራ ክንድ ድል እናረጋግጣለን ብለዋል።