ቀጥታ፡

የላይኛው ተፋሰስ አገራት የናይል ወንዝ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በጋራ ሊቆሙ ይገባል

ነሐሴ 19 ቀን 2013 (ኢዜአ) የላይኛው ተፋሰስ አገራት የናይል ወንዝ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በጋራ መቆም እንዳለባቸው ከአገራቱ አምባሳደሮች ጋር የተወያዩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።

ኢትዮጵያ በናይል ተፋሰስ አገራት መካከል ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም መርህ እንዲሰፍን ጠንካራ አቋም በመያዝ ከተቀሩት የተፋሰሱ አገራት ጋር በቅርበት ስትሰራ መቆየቷን አስታውሰው፤ ይህንኑ ማጠናከር የሚያስችል የምክክር ጉባኤ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የናይል አጠቃላይ ስምምነት ማዕቀፍ ያልፈረሙና ያላፀደቁ የላይኛው ተፋሰስ አገራት እንዲፈርሙና እንዲያፀድቁ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል። 

"ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሠላምና መረጋጋት እጦት መንስኤ አይደለም፤ ይልቁንም የቀጣናውን ትስስርና ትብብር ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ ያለው ነው" ብለዋል።

"በመሆኑም ኢትዮጵያ የላይኞቹ የተፋሰሱ አገራት የአፍሪካ ኅብረትን የአደራዳሪነት ሚና በመደገፍ ድምጽ እንድትሆኑ ትጠይቃለች" ሲሉ ገልጸዋል።

ግብጽና ሱዳንም በድርድሩ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የተፋሰሱ አገራት ሊያበረታቱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የላይኛው ተፋሰስ አገራት ምክንያታዊ የሆነውን የናይል ወንዝ ተጠቃሚነት መብት ለማስጠበቅ በጋራ መቆም እንደሚገባቸው ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ጉዳዩን ለአገራቱ የምታቀርበው በዚሁ አግባብ መሆኑን አብራርተዋል።

"የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ከቱኒዚያ ጋር በመሆን በናይል ወንዝ ላይ ያለንን ታሪካዊ ተጠቃሚነት ያላገናዘበ ውሳኔ ለመስጠት ጉዳዩን የጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ለማድረግ ግፊት እያደረጉ ነው" ብለዋል።

ቱኒዚያ ለግብጽ ተገቢ ያልሆነ ድጋፍ ለማድረግ ለፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ ቢደረግም በድጋሚ ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጓን ገልጸው፤ ውሳኔው ከተወሰነ ሁሉንም የላይኛው ተፋሰስ አገራት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሊያስገባ ስለሚችል ሃሳቡን ለመቀልበስ መተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አምባሳደር ሬድዋን አክለውም የቱኒዚያ አካሄድ በአፍሪካ ኅብረት አስተባባሪነት እየተካሄደ ያለውን የሶስትዮሽ ድርድር ጥረት የሚያደናቅፍ መሆኑን ገልጸው፤ አገራቱ ኒውዮርክ ለሚገኙት ሚሲዮኖቻቸው ይህንኑ እንዲገልጹላቸው ጠይቀዋል።

የላይኛው ተፋሰስ አገራት አምባሳደሮች በበኩላቸው ድንበር ተሻጋሪ ሃብቶችን ለጋራ ልማት ለማዋል ትብብር እንደሚያስፈልግ፤ የአፍሪካን ጉዳይም በአፍሪካዊያን መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

"በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን የናይል ወንዝ የሚገኘው በአፍሪካ አህጉር ነው፤ መፍትሄውም በዚሁ አህጉር ሊበጅለት ይገባል፤ ናይልም በጋራ የምንጠቀምበት ሊሆን ይገባል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም