በአገር ሕልውና ትግሉ ምሁራን የአርበኝነት መንፈስ እንዲላበሱ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በአገር ሕልውና ትግሉ ምሁራን የአርበኝነት መንፈስ እንዲላበሱ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 19-2013 (ኢዜአ) በአገር ሕልውና ትግል ውስጥ ምሁራን የአርበኝነት መንፈስ ተላብሰው ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር 'በአገር ግንባታ የምሁራን ሚና' በሚል ያዘጋጀው አገር አቀፍ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ዑርቃቶ ኢትዮጵያ ከድህነት ጠላቷ ባለፈ የዕጅ አዙር ሃይላት አበይት ጠላቷ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የተዘረጉ የዕጅ አዙር ሃይላትን ለመመከት የምሁራንን የተለየ ጥበብ፣ ዕውቀትና ዕይታ እንደሚጠይቅ አመላክተዋል።
ምሁራን ቀደም ብሎ በዲጂታል ዲፕሎማሲ፣ በሕዳሴ ግድብና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉልህ ሚና እንደነበራቸው ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ለገጠማት አሁናዊ ፈተናም የእነርሱ ልዩ ጥረት እንደሚሻ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ እድገት የተቀረውን አፍሪካ ለመቆጣጠር ስጋት ይሆናል በሚል የውጭ ሃይሎች ስውር እጃቸውን እንደሚያሳርፉ አስታውሰው፤ የዕጅ አዙር ጫናውን የሚመክት የማንቃት ስራ ከምሁራን ይጠበቃል ብለዋል።
ውስጣዊ ችግሮችን ከተሻገርን ውጫዊ ሃይላትን መቋቋም ይቻላል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ምሁራን ለአሁናዊም ሆነ ለቀጣይ ፈተናዎች በተቀናጀ መንገድ በአገር ሉዓላዊነትና አንድነት ላይ በትኩረት እንዲሰሩ አደራ ብለዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ በበኩላቸው አሸባሪው የህወሓት ቡድን በቀሰቀሰው ጦርነት ከፍተኛ ሠብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት መከሰቱን አውስተዋል።
በአገር ጉዳይ ችግር ሲከሰት ገለልተኛ መሆን እንደማይቻል ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ካጋጠማት ችግር እንድትወጣ ምሁራን ተጨባጭ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚጠቅባቸው ተናግረዋል።
በመድረኩ የመወያያ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ ምሁራንም ኢትዮጵያ እያደረገች ባለው የሕልውና ትግል ምሁራን የአርበኝነት መንፈስ መላበስ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ምሁሩ ዶክትር ከይረዲን ተዘራ በአብዮቱ ዘመን የነበሩ ጥቂት ምሁራን ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደነበራቸው አስታውሰዋል።
የተማረ የሰው ሃይል በበረከተበት በአሁኑ ወቅት ግን የምሁራን ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን ገልጸው፤ 'ፖለቲካና ኤሌክትሪክ በሩቁ' ከሚለው ብሂል ወጥቶ ከዳር ተመልካችነት ወደ ተዋናይነት መሻገር እንደሚገባ ገልፀዋል።
በፖለቲካ ጉዳይ ገለልተኛ መሆን ቢቻልም በአገር ጉዳይ ግን ወገንተኛ መሆን ተገቢ ነው ብለዋል።
እናም የክተት አዋጅ በታወጀበት፣ኢትዮጵያ ውስጣዊና ውጫዊ አደጋዎች በገጠሟት በዚህ ወቅት ምሁራን የአገር ሕልውናን ለመታደግ በሚደረገው ትግል የአርበኝነት መንፈስ ልንላበስ ግድ ይላል ነው ያሉት።
ምሁራን በአገር ግንባታ ሂደት የማይተካ ሚና እንዳላቸው ያብራሩት ዶክተር ዲማ ነገዎ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከ20ኛው ከፍለ ዘመን ጀምሮ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን በመታገል ጉልህ ሚና ነበራቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከድህነትና ኋላቀርነት ተላቃ ወደፊት መራመድ ያልቻለችው በምሁራን ማነስና በቴክኖሎጂ፣ በችግር ፈች ምርምርና ፈጠራ ረገድ ሚናቸውን ባለመወጣታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በደርግና በኢህአዴግ ዘመን ምሁራን በፀረ መንግስትነት ተፈርጀው ሚናቸውን እንዳይወጡ ጫና እንደተደረገባቸው፣ ለስደትና ለሞት እንደተዳረጉም አስታውሰዋል።
ይህም በአገር ግንባታ ላይ አሉታዊ ተዕጽኖ እንደነበረው አብራርተዋል።
ዛሬም ኢትዮጵያን ከገጠማት ውስብስብ ችግር ማራመድ የምንችለው በምሁራን ጥረት ነው ያሉት ዶክተር ዲማ፤ ምሁራን ከእርስ በርስ ሽኩቻ ተላቀው ሊደራጁና ተቋማትን ሊመሰርቱ፣ በጥናት ምርምር መንግስትን ሊያግዙ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለውጥ የማይፈልገው አሸባሪው ቡድን ባደረሰው ጥቃት መልከ ብዙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያ አሉታዊ ውጤት መከሰቱን ምሁራኑ ገልጸዋል።
ምሁራን ለሕዝብ ድምጽና ጆሮ በመሆን፣ ፍትህ ከሚሹ ዜጎች በመወገን፣ እውነትን መናገርና ሀሰትን መጋፈጥ ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል።
ለብሔራዊ ጥቅም በመቆም አገር ለማፍረስ የሚሰራውን አካል መዋጋት ወቅቱ የሚጠይቀው የምሁራን ድርሻ እንደሆነም ተናግረዋል።