ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ ህወሀት የሀገርና የህዝብ አንድነትን ለመናድ ከሚያሰራጨው የሀሰት ወሬ ራሱን መጠበቅ አለበት -- ምሁራን

ጭሮ፣ ነሐሴ 19/2013(ኢዜአ) ህብረተሰቡ ህወሓት የሀገርና የህዝብ አንድነትን ለመናድ ከሚያሰራጨው የሐሰት ወሬ ራሱን መጠበቅ እንዳለበት የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ ምሁራን አስገነዘቡ፡፡

ኢዜአ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ያነጋገራቸው ምሁራኑ "ህወሓትና ሸኔ በጥምረት ኢትዮጵያን ለማፍረስ መስማማታቸው ሽብርተኝነታቸውን ያጠናከሩበት ስለመሆኑ ማሳያ ነው " ብለዋል።

በኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ የተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ ሁሴን የሱፍ የኢትዮጵያን እድገት መሰረት የሚያስይዙ የህዳሴው ግድብን ጨምሮ በርካታ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸው እረፍት የነሳቸው የሀገር ጠላቶች ከውስጥና ከውጭ ተደራጅተው እያጠቁን ነው።

ሕወሓትና ሸኔ በሀሰት ወሬ የሀገሪቱን ገፅታ ለማበላሸትና የህዝብን ሰላም ለማደፍረስ የጀመሩትን ጦርነት ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ማውገዝና ማጋለጥ እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል፡፡ 

አንዳንድ የውጭ መንግስታትም ቢሆኑ የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማስፈፀም ሲሉ ለአሸባሪ ቡድኖቹ  ድጋፍ መስጠታቸው አግባብ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

አሸባሪው የህወሀት ቡድን የሀገርና የህዝብን አንድነት ለመናድ ከሚያሰራጫቸው የሀሰት ወሬዎች ህብረተሰቡ ራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

በተለይም ወጣቱ ሀገር ለማፍረስ የተነሱ የአሸባሪ ቡድኖችን  ሴራ በመገንዘብ ራሱን በመጠበቅና ተባባሪና ወሬ አቀባዮችን በማጋለጥ ሀገሩን ከጥፋት ሊጠብቅ እንደሚገባ አሳስበዋል ።

"ኢትዮጵያ አንድ የሚያደርጋት መንግስት እንጂ በውሸት መሰረት ላይ ተዋቅሮ የሀገር አንድነት ለመበተን የሚመጣ አካል አያስፈልጋትም" ያሉት አቶ ሁሴን "ኢትዮጵያዊያን መጨረሻችን የእነ የመንና ሊቢያ እጣ እንዳይሆን ከውሸት መረጃ መጠበቅ ይኖርብናል" ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡


"የህወሓት ቡድን ቀድሞ በዘረፈው ገንዘብ በውጭ የብዙሀን መገናኛዎች  የኢትዮጵያን ስም የሚያጠፉ መረጃዎችን የሚያሰራጭበት ትልቁ አላማ ህዝብን እያወናበደና ሀገር እየዘረፈ የመኖር ምኞቱን ለማሳካት የያዘውን አጀንዳ ለማስፋፋት ነው" ያሉት ደግሞ  የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አሚን መሀመድ ናቸው፡፡ 

ዶክተር አሚን አክለውም ህወሓትና ሸኔ በጥምረት ኢትዮጵያን ለማፍረስ  መስማማታቸው ሽብርተኝነታቸውን ያጠናከሩበት ስለመሆኑ ማሳያ ነው" ብለዋል ።

"የሽብር ቡድኖቹ በተለያየ አቅጣጫ ለዘመናት የኢትዮጵያን ህዝብ ሲያደናግሩ ኖረዋል፤ ከዚህ በኋላ ግን ሊኖሩ አይችሉም " ሲሉም ሽብርተኞቹን አውግዘዋል።  

"ቡድኖቹ በሚያሰራጩት የውሸት ፕሮፓጋንዳ የብዙዎች ወጣቶች ህይወት እንዲያልፍ ምክንያት ሆኖ ኖሯል" ያሉት ዶክተር አሚን ወጣቶች የውሸት መረጃዎችን በመቀባበል ወዳልተገባ መንገድ ከመሄድ እንዲጠነቀቁ መክረዋል፡፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትውልድ የሚቀረፅባቸው ስፍራዎች እንደመሆናቸው ምሁራን ትዊተር በመክፈት በኢትዮጵያ ያለውን  እውነት ለዓለም ማሳየትና ማሳወቅ እንዲሁም የአሸባሪዎችን ተግባር ማጋለጥ እንደሚጠበቅባቸው  ዶክተር አሚን አስገንዝበዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም