ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊቷ ለወላጅ አባታቸው ተስካር ማውጫ የተዘጋጀ 100 ሺህ ብር ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድጋፍ አደረጉ

ነሐሴ 19 ቀን 2013 (ኢዜአ) በጀርመን አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊቷ  ወይዘሮ ሌንሳ ተሾመ ለወላጅ አባታቸው ተስካር ማውጫ የተዘጋጀ 100 ሺህ ብር ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲውል አደረጉ።

ለዚህም ከግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የምስጋና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

ወይዘሮ ሌንሳ ነሐሴ 17 ቀን 2013 ዓ.ም የአባታቸው ሰባተኛ ሙት ዓመት ተስካር ለማውጣት ቢዘጋጁም ድግሱን በማስቀረት ለዝግጅቱ የታሰበው የ100 ሺህ ብር ወጪ ለግድብ ግንባታ እንዲውል ገንዘቡን ገቢ ማድረጋቸው ዛሬ ተገልጿል።

ወይዘሮ ሌንሳ የምስክር ወረቀቱን ዛሬ ከጽሕፈት ቤቱ በተቀበሉበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ለኢትዮጵያዊያን ልዩ ትርጉም ያለው ግድቡ ኢትዮጵያዊያን ከተባበሩ በራሳቸው አቅም የትኛውንም ተግባራት ውጤታማ ማድረግ እንደሚችሉ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የዳያስፖራ ማሕበረሰብ ለግድቡ ግንባታ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የሚያስደስት መሆኑን አንስተው፤ ግንባታው ከፍጻሜ እስኪደርስ ድጋፉ ተጠናከሮ እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል።

የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊቷ ያደረጉት ድጋፍ አርዓያነት ያለው ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል።

በቀጣይም መሰል ድጋፎች በማድረግ ግድቡን እስከ ፍጻሜው መደገፍ እንደሚገባም ነው ዶክተር አረጋዊ ያሳሰቡት ።

የጽህፈት ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብረሀም፤ እስካሁን ባለው ጊዜ በተለይ ህጻናት የልደታቸው ወጪ ለግድቡ ግንባታ እንዲውል መስጠታቸውን አስታውሰዋል።

ነገር ግን ለሙት ዓመት መታሰቢያ የተዘጋጀ ገንዘብን ለግድቡ ግንባታ በመስጠት በኩል ወይዘሮ ሌንሳ ፈር ቀዳጅ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ ከዳያስፖራዉ ማሕበረሰብ 134 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ መቻሉም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም