ቀጥታ፡

በአሸባሪው ህወሓት ማደናገሪያ ተታለው የትግራይ ወጣቶች ወደ ጦርነት መግባት የለባቸውም

ነሐሴ 19/2013(ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት "ማደናገሪያ ተታለው ወጣቶች ወደ ጦርነት እንዳይገቡ" ሲሉ ወደ አፋር ክልል በመግባት በውጊያ ተሰልፈው የቆሰሉ የትግራይ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

ወጣቶቹ "ሥራ ታገኛላችሁ" ተብለው በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ተታለው በሶስት ቀን ስልጠና ብቻ ወደ ጦርነት መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

መቀሌ ከተማ ተወልዶ ማደጉን የሚናገረው ወጣት በሪሁን ወልዱ የድንጋይ ጫኝና አውራጅ ሠራተኛ ሆኖ ሲሰራ መቆየቱን ይገልጻል።

በዚሁ ሥራውም ከራሱ አልፎ ቤተሰቡን በመርዳት ኑሮውን ይመራ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ የተኩስ አቁም በማድረግ ከመቀሌ መውጣቱን ተከትሎ በአሸባሪው ቡድን "ሥራ ታገኛለህ" በሚል የሐሰት ዜና ተታሎ በሦስት ቀን ሥልጠና ጦርነት ውስጥ ተሳትፎ መቁሰሉንም ይናገራል፡፡

በአፋር ልዩ ኃይል እገዛም ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ጥሩ እንክብካቤ እየተደረገለት ይገኛል፡፡

የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነች የነገረችን የቅሳነት ማስሼ በበኩሏ "ሥራ ታገኝያለሽ" በሚል የውሸት ምዝገባ ተታላ ወደ ጦርነት ማምራቷን ተናግራለች፡፡

በዚህም በአራት ቀን ሥልጠና ያለፍላጎቷ ወደ ጦርነት ገብታ ጉዳት እንደደረሰባት በሀዘን ትናገራለች ፡፡

ወጣት ክብሮም ገብረማርያም በመቀሌ ከተማ በታክሲ ረዳትነት ሙያ በመሰማራት ራሱንና ወላጆቹን በመርዳት ላይ እያለ በአሸባሪው ቡድን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ተታሎ ወደ  ጦርነት መግባቱንም ነው ያጫወተን።  

በመቀሌ አካባቢ ኩሃ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ሦስት ቀን ሥልጠና ተሰጥቶት ወደ አፋር ክልል መላኩን ይገልጻል። በዚያም ጉዳት ደርሶበት ቁስለኛ ሆኗል፡፡

የትግራይ ወጣቶች "ከእኛ ብዙ ነገር ሊማሩ ይገባል" ሲሉ መልዕክት ያስተላለፉት ወጣቶቹ፤ በአሸባሪው ቡድን የሐሰት ጥሪ ተታለው ለጦርነት መማገድ እንደሌለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአፋር ክልል ዱብቲ ሪፈራል ሆስፒታል የድንገተኛ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ኑሩ ሰይድ እንዳሉትም፤ ቁስለኞቹ ወደ ህክምና ተቋሙ ከገቡ ጊዜ ጀምሮ በሙያቸው አስፈላጊውን ትብብር እያደረጉላቸው ነው።

ለቁስለኞቹም ከፍተኛ ቀዶ ህክምናን ጨምሮ በጉዳታቸው ልክ አስፈላጊው እርዳታ እንደተሰጣቸውም ነው ዶክተር ኑሩ የሚገልጹት።

በዚህም ሦስቱ ወጣቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ማገገማቸውን ገልጸው፤ ቀሪዎቹም በአጭር ጊዜ ወደ ጤንነት እንደሚመለሱም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በርካታ ህጻናትንና ወጣቶችን በማታለል ለጦርነት በመማገድ ህይወታቸው በአጭር እንዲቀጭ እያደረገ መሆኑንም  ወጣቶቹ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም