ቀጥታ፡

የሀገር ህልውናን ለማስከበር በየዘርፉ የተጀመረው የጋራ ትግል ተጠናክሮ መቀጠል አለበት

ዲላ፣ ነሀሴ 19/2013 (ኢዜአ)- " ህወሀት ከከፈተብን ጦርነት በተጓዳኝ በውጭ ሀይሎች በዲፕሎማሲና በምጣኔ ሃብት የተደቀነብንን ጫና በመመከት የሀገርን ህልውና ለማስከበር በየዘርፉ የተጀመረው የጋራ ትግላችን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ሲሉ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ። 

ኢዜአ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙርያ ያነጋገራቸው ምሁራኑ የምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነት መጨረሻው ሀገር ማፍረስ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሃብት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ዳዊት ሃዬሶ "ኢትዮጵያዊያን የተጋረጠብንን የህልውና ትግል ለመቀልበስ ሆ ብለን በጋራ መነሳታችን በሀገር ጉዳይ እጅ እንደማንሰጥ በድጋሚ ያሳየንበት ነው" ብለዋል።

"በህወሀት ከተከፈተብን ጦርነት በተጓዳኝ በውጭ ሀይሎች በዲፕሎማሲና በምጣኔ ሃብት የተደቀነብንን ጫና በመመከት የሀገርን ህልውና ለማስከበር በጋራ የጀመርነው ትግል ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ሲሉ አስገንዝበዋል።

መንግስት የውስጥና የውጭ ጫናዎችን ለመቋቋም ከወዳጅ ሀገራት ጋር ያለውን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ማጠናከሩ ጫናዎችን ለመቋቋም አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ እንደ ቱርክ ካሉ ከጋራ ተጠቃሚነት ውጭ በሉአላዊነት ላይ ገብተን እንፈትፍት ከማይሉ ሀገራት ጋር ወዳጅነት ማጠናከር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

ዶክተር ዳዊት በማያያዝ የምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነት መጨረሻው ሀገር ማፍረስ መሆኑን ጠቁመው "በአፍጋኒስታንና ሊቢያ የደረሰውን ማየት በቂ ነው " ሲሉ  በማሳያነት አንስተዋል።

ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ አሻንጉሊት መንግስት የማቋቋም ህልማቸው እንዳይሳካ በየዘርፉ የተደቀነብንን ጦርነትና ጫና በጋራ ልንመክት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"የተጋረጠብን ጫና ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ከመቋቋም ውጭ አማራጭ የለንም" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የአስተደደር ጥናት ኮሌጅ መምህር መሳይ ፍቅሩ ናቸው።

በዘመናዊው ዓለም ከግንባር ጦርነት ባልተናነስ መልኩ የኢኮኖሚ ጫና የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ከቱርክ ጋር ስምምነት መፈጸሙ ጠቀሜታው ብዙ መሆኑን ተናግረዋል።

መምህር መሳይ አክለው ኢትዮጵያ ገበያ መር በሆነ ነጻ ኢኮኖሚ የምትመራ ሃገር ብትሆንም በህወሀት የፖለቲካ አሻጥር ገበያውን ወደ አሻቸው የሚዘውሩ ግለሰቦችና የብሔር መልክ ያላቸው የንግድ ተቋማት መፈጠራቸውን ጠቁመዋል።

የምርት አቅርቦትን ከማሳደግ ጎን ለጎን ለፖለቲካ አሻጥር ዋጋ በማናር የህዝብን ቁጣ ለመቀስቀስ በሚሰሩ የንግድ ድርጅቶች ላይ የሚወሰደው ቁጥጥርና ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም