ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በኮቪድ-19 እና በሌሎች ጫናዎች ውስጥ ሆና ከቡና ንግድ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ችላለች

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 19/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ኮቪድ-19ን ጨምሮ ሌሎች የውስጥና የውጭ ጫናዎች ቢኖሩባትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከቡና ምርት ከፍተኛ የተባለውን ገቢ ያገኘችበት እንደሆነ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገልጿል።
ባለሥልጣኑ በ2013 በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃጸም ላስመዘገቡ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ላኪ ድርጅቶችና ተቋማት እውቅና ሰጥቷል።

በቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶችን ላኪ ድርጅቶች በተጨማሪም አቅራቢዎች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና አርሶ አደሮች እውቅና ተችሯቸዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ155 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርትን አምራቹን ከላኪው በማስተሳሰር የተሻለ አፈፃፀም መመዘገቡም ተገልጿል።

በተጓዳኝም በበጀት ዓመቱ የቡናን ምርት ለማሳደግ ከ1 ቢሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ተተክለዋል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በ2013 በጀት ዓመት ከቡና የወጪ ንግድ 907 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

ይህም አገሪቷ በኮቪድ-19 እንዲሁም በውስጥና በውጭ ጫናዎች ውስጥ ሆና ከፍተኛ የተባለውን ገቢ ያገኘችበት፤ ቡናም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዋልታ መሆኑን ያስመሰከረበት ዘመን ነው ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቡና ምርት ካላት አቅም አንፃር ከዚህም በላይ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ተናግረዋል።

ለቡና ምርት እድገት የተሰጠው ትኩረት የተዘመረለትን ያህል አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ ያም ሆኖ በበጀት ዓመቱ የግብይት ሥርዓቱን በማሻሻል ችግሮችን ተቀራርቦ የመፍታት ባህሉ እያደገ በመምጣቱ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

ለኢዜአ ያነጋገራቸው እውቅና የተሰጣቸው ድርጅቶች ተወካዮችም እውቅናው የልፋታቸውን ዋጋ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም አገሪቷ ከቡና ምርት ለማግኘት ያቀደችውን ግብ ለማሳካትና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

አቶ ደረጄ ዳዲ የኦሮሚያ ቡና ማኅበር ስራ አስኪያጅ "ሂደቱ በጣም ደስ የሚል ነው፤ እንዳንዱ ድርጅት የልፋቱን ዋጋ ሲያገኝ የበለጠ ለሚቀጥለው ጊዜያት የበለጠ ተግተን እንድንሰራ ለድካማችን ዋጋ መሰጠቱ በጣም ደስ ብሎናል።"

ከዳየ ቦንሳ ቡና ላኪዎች አቶ ከነዓን አሰፋ "ሪኮግናይዝ መደረጋችን በዚህ ደረጃ በጣም ደስ የሚል ነገር ነው፤ የሚያበረታታ ነገር ነው፤ እኛም እንደ ድርጅት ላይ መንግስት አሁን እንደተባለው 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ጄኔሬት ለማድረግ ነው ሃሳቡ ያንን ኮንትሪቢዩት ለማድረግ እንድንነሳሳ ይህ እውቅና ለእኛ ድጋፍ ይሆነናል።"

ባለሥልጣኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶች አጠቃላይ የወጪ ንግድ 927 ዶላር ገቢ አግኝቷል።

በ2014 በጀት ዓመትም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት እቅድ መያዙን ባለሥልጣኑ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም