ሃምሳ አጫጭርና የሙሉ ጊዜ ቴአትሮች ለተመልካቾች ይቀርባሉ - ኢዜአ አማርኛ
ሃምሳ አጫጭርና የሙሉ ጊዜ ቴአትሮች ለተመልካቾች ይቀርባሉ
አዲስ አበባ ነሃሴ 19/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማኅበር በኢትዮጵያ ቴአትር የተጀመረበትን 100ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ 50 አጫጭርና የሙሉ ጊዜ ቴአትሮችን ለተመልካቾ ሊያቀርብ ነው።
ቴአትሮቹ ከነሐሴ 21 እስከ 25 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተመረጡ ቴአትር ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶችና የባሕል ማዕከላት ለተመልካች ይቀርባሉ ተብሏል።
ከቴአትር ቤቶች ብሔራዊ እና አገር ፍቅር ቴአትር ቤቶች፤ እንዲሁም የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባህል ማዕከላት መመረጣቸው ተገልጿል።
አምባሳደር፣ አዶት፣ ሴንቸሪ እና ኤድናሞል ሲኒማ ቤቶችም ቴአትሮቹ እንዲቀርቡባቸው ተመርጠዋል።
በመርኃ ግብሩ አባጅፋር ለመፎና አባ ኢሊማ የተሰኙ በኦሮምኛ ቋንቋ የተሰሩ ቴአትሮች የሚቀርቡ ሲሆን ባቢሎን በሳሎን ቴአትርም በኦሮምኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለእይታ እንደሚቀርብ ታውቋል።
የመርኃ ግብሩ አስተባባሪና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት መምህር አንተነህ ሰይፉ ቴአትሮቹ ከዚህ ቀደም ለመድረክ የበቁ፣ በመታየት ላይ ሚገኙና አዳዲሶችም መሆናቸውን ገልጿል።
100 ቴአትሮችን ለማቅረብ ታስቦ የነበረ ቢሆንም በፋይናንስ ችግር ምክንያት 50 ቴአትሮች ብቻ ለተመልካቾች ለእይታ እንደሚቀርቡ ተናግሯል።
ተመልካቹ ቴአትሮቹን እንዲመለከት የመገናኛ ብዙኃን መረጃውን የማስተላለፍ ሥራ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርቧል።
በኢትዮጵያ ቴአትር የተጀመረበትን 100ኛ ዓመት በማስመልክት ሚያዚያ 5 ቀን 2013 ዓ.ም የቴአትር ማነቃቂያ መርኃ ግብር በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል።