ቀጥታ፡

ሕዝቡ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 2 ቢሊዮን 49 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል

አዲስ አበባ ነሃሴ 19/2013 (ኢዜአ) በተያዘው ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከኅብረተሰቡ 2 ቢሊዮን 49 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው በተያዘው ዓመት ከኅብረተሰቡ የተሰበሰበው ገንዘብ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ እስካሁን ከተደረገው ድጋፍ ከፍተኛው ነው።

የጽህፈት ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብረሀም እንደገለጹት በቀደሙት ጊዜያት በዓመት ይሰበሰን የነበረው ከፍተኛው ገንዘብ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በልጦ አያውቅም፡፡

በተያዘው ዓመት በኅብረተሰቡ ዘንድ የታየው ከፍተኛ ተሳትፎ ለገቢው መጨመር ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

"ግድቡ የእኔ ነው" በሚል በሞባይል አጭር የፅሁፍ መልዕክት 8100- A በተደረገ አስተዋጽኦ 132 ሚሊዮን ብር የተገኘ ሲሆን ከዳያስፖራው ተሳትፎ ደግሞ 134 ሚሊዮን ብር እንደተገኘ ተገልጿል፡፡

3ኛው ዙር 8100-A አጭር የሞባይል መልዕክት በብሔራዊ ቤተመንግስት በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የካቲት 25 ቀን 2012 በይፋ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም