ቀጥታ፡

ዳግም ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ሀገርን ለማዳን መዝመት ያስደስታል

ድሬዳዋ ነሐሴ 19/2013 (ኢዜአ) ዳግም ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ሀገርን ለማዳን መዝመት ያስደስታል ሲሉ የገለጹት ከድሬዳዋ ወደ ጦር ግንባር የተንቀሳቀሱ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ናቸው።

ከድሬዳዋ ከ200 በላይ የሚሆኑ የቀድሞ የሠራዊቱ አባላት ትላንት ወደ ግንባር ተሸኝተዋል፡፡

የቀድሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላቱ ኢትዮጵያን ለማዳን ህይወታቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ለኢዜአ አስታውቀዋል።

በ10 አለቃነት ማዕረግ ሰራዊቱን ያገለገሉትን ሁሴን መሐዲ ሠራዊት ዳግም ሊቀላቀሉ ተነስተዋል።

ከመጀመሪያው ግዳጅ መልስ በድሬዳዋ በኮንስትራክሽን ባለሙያነት ሕይወታቸውን ሲመሩ ቆይተው።

ኢትዮጵያ በአሸባሪው ቡድን ህወሃት እንደማትፈርስ ሙሉ እምነት አለኝ "ያሉት የአስር አለቃ ሁሴን ሀገር ስትፈርስ ዝም ብሎ የሚያይ  ልብ  የሌላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ትላንት ዳግም ክተት ብለው ወደ ግንባር ለመዝመት ከድሬዳዋ ተሸኝተዋል ።

''ሌት ተቀን ሀገርን ለማዳን ህይወቱን እየሰጠ ከሚገኘው ሠራዊት ጎን በመቆም ሀገር ለማዳን መዝመት ያስደስታል፡፡'' ብለዋል።

''ከዘመቻው በኋላ በህይወት ከተመለስኩ ሰላም በሆነችው አገሬ እየሰራሁና ጥሩ ታሪክ ለልጄ እየነገርኩት እኖራለሁ'' ሲሉ ተሰናብተዋል፡፡

''ቤተሰቤን አሳምኜ፣ ልጄን ለሰው ወዳዱ የድሬዳዋ ሕዝብ አደራ ብዬ ተጉዣለሁ፤ በድልም እመለሳለሁ'' የቀድሞ ወታደር ሞላ አስማረው ነው፡፡

''ከሀገር በላይ ምንም የሚቀድም ነገር ስለሌለ ሀገሬን ለማዳን ዳግም ዘምቻለሁ'' ሲል አክሏል፡፡

ሌላው የቀድሞ ሰራዊት ሞላ ታምራት የሹ በበኩሉ ''የሀገሬን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ሕይወቴን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ'' ብሏል።

''ሕይወታችንን ለሀገራችን ክብርና ሉዓላዊነት መከበር ለመስጠት ወደ ግንባር ዘምተናል'' በማለት የእሱና የጓደኞቹን ጽኑ አቋም ገልጸዋል።

ሌላው ተፈሪ ሰብስቤ ከ13 ዓመታት በፊት ታንከኛ ነበሩ፤ ኢትዮጵያን የማዳን ዘመቻውን ለማሳካት የሲቪል ሕይወታቸውን ትተው ዳግም ሰራዊቱን ለመቀላቀል ተነስተዋል፤፡፡

ወታደሩ ዛሬም እምነታቸው አንድና ጽኑ ነው፤ ''ሀገሬ አትፈርስም፤ ወያኔ ይፈርሳል፤ ኢትዮጵያ አንድነቷ ፀንቶ ለዘዓለም ትኖራለች!'' ብለዋል፡፡

''ከአያት፣ ከአባትና እናቶች የተረከብነው ታላቅና የታፈረች ሀገር ለትውልድ የማስረከብ ታሪካዊ ኃላፊነታችንን በስኬት እንወጣለን''ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ናቸው፡፡

''ሀገርን ለማዳን ወደ ግንባር የተነሳችሁ ተመላሽ የሠራዊት አባላት ለሀገር ለምትከፍሉት ዋጋ የድሬዳዋና የኢትዮጵያ ሕዝብ ይኮራባችኋል'' ብለዋል፡፡

የቀድሞ ወታደሮቹ ከአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት ወደ ግንባር እየተመሙ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆንና ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ሀገራቸውን እንደሚያድኑም እምነታቸውን ገልጸዋል፤ ምክትል ከንቲባው፡፡

የአስተዳደሩ ፍትህ፣ ፀጥታና የሕግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሣ ጠሃ ''ኢትዮጵያችን አሁን የሁላችንንም ትብብር ትፈልጋለች፤ አንድነታችንን አጽንተን የሀገርን ታላቅነት እናስከብራለን'' ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደርና ሕዝብ ለሠራዊቱ እያደረገ ከሚገኘው የስንቅ ዝግጅት ባሻገር፤ የድሬዳዋ ልዩ ኃይልን ወደ ግንባር መላኩ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም