ቀጥታ፡

በሙስሊም ማህበረሰብ ዘንድ ያለው አንድነት እንዲጠናከር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ  ነሀሴ 5/ 2010 በሙስሊም ማህበረሰብ ዘንድ ያለውን አንድነት እንዲጠናከር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ ። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ የውይይት መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ ዑላማዎች፣ምሁራንና የዕምነቱ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን የአንድነትና የትብብር መድረክ ተካሂዷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአገሪቷ ያሉ ሙስሊሞች የገጠማቸውን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ዘጠኝ አባላት ያሉት የጋራ ኮሚቴ መቋቋማቸው ይታወሳል። ኮሚቴው ከእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴና ከገለልተኛ አካል የተወጣጣ ነው። ኮሚቴው በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ አሁን ላይ ያሉ ልዩነቶች እንዴት ይፈቱ?፣ በቀጣይ ምን መደረግ አለበት? በሚሉት ሀሳቦች ዙሪያ ተወያይቷል። የጋራ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የእስልምና አስተምህሮ ትኩረት የሚያደርገው አንድነትን፣ወንድማማችነትን መተባበርና መከባበርን ነው አንጂ  መለያየትን አይደለም። ''በአሁኑ ወቅት ወደ አንድነት ለመምጣት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል'' ያሉት ሀጂ ዑመር ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል ልናመሰግናቸው ይገባል ብለዋል። ስለ ሠላም በቁርዓን ላይ በግልጽ ተቀምጧል ወደ ተግባር መቀየር ደግሞ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ''ሞትና እርጅና ብቻ ነው መድሃኒት የሌለው'' ያሉት ሰብሳቢው አንድነታችንን የከለከለውን በሽታ ለይተን መፍቴሄ ልናመጣ ያስፈልጋል ሲሉም አዕንኦት ሰጥተዋል። በተለይ ወላጆች ለልጆቻቸውና ወጣቶች በመልካም ስብዕናና በአንድነት መንፈስ እንዲታነጹ መሥራት እንደሚያሻም አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሀጂ ሙሀመድ አሚን ጀማል በበኩላቸው የእምነቱ ምሁራን፣አባቶች በተፈጠሩ ስህተቶች የታየው መከፋፋል ከመሰረቱ እንዲፈታ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። የጋራ ኮሚቴው ጸሀፊ ዶክተር እድሪስ መሐመድ እንደገለጹት፤ኮሚቴው ለሙስሊም ማህበረሰቡ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የእምነቱ ተከታዮችን በማስተባበር መጅሊሱ የሚቋቋምበት የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት፣የመጅሊስ አወቃቀርና አደረጃጀት ሰርቶ ማቅረብ እንዲሁም የሙስሊሙ ማህበረሰብ አንድነት እንዲጠበቅ የማድረግ ኃላፊነትን ተቀብሎ እየተንቀሳቀሰ ነው። የሙስሊሞችን አንድነት ጠብቆ ለማስቀጠል በይዘትም በአደረጃጀትም ጠንካራና ሁሉን አቀፍ ድርጅት መቋቋም ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ድርጅቱን ማቋቋም የሚያስችል የሕግና አደረረጃጀት የሚያመላክት ምክረ ሀሳብ  ማቅረብ ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል። በአገሪቷ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የእምነቱ ተከታይ ቢኖርም በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ያላቸው ተሳትፎ ወደ ኋላ የቀረ ነው ይሄንን ለመፍታት በጥናት የተደገፈ ጥረት እንደሚከናወን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም